በተለያዩ አካባቢዎች ለኮሮና መከላከል የሚያግዙ በርካታ ድጋፎች ተደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
በተለያዩ አካባቢዎች ለኮሮና መከላከል የሚያግዙ በርካታ ድጋፎች ተደረጉ
ዲላ /ሀዋሳ /ባህርዳር /ማይጨው /ጋምቤላ /ሶዶ / ኢዜአ ሚያዝያ 5/2012 ዓም. በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች የኮረና ቫይረስን ለመከላከል የሚደረጉ ጥረቶችን የሚያግዙ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ከየቦታው የተገኙ መረጃዎች አመላከቱ ።
በዲላ ከተማ ለ265 በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የቀለብና የንጽህና መጠበቅያ ቁሳቁሶች ድጋፍ ተደርጓል ።
የዲላ አማኑኤል ህብረት ቤተክርስቲያን ለ250 በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የምግብና የንጽህና መጠበቅያ ቁሳቁሶች ድገፍ ማድረጓን የቤተክርሲቲያኗ የልማት ማህበር ዳይሬክተር አቶ ክንድሁን ወርቃለማሁ ለኢዜአ ተናግረዋል።
ድጋፉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሸን መከሰቱን ተከትሎ በቤት የሚውሉ ዜጎች ለችግር እንዳይዳረጉ በማሰብ መሆኑን ጠቁመዋል።
ቤተ ክርስቲያኗ ለድጋፉ ከ3 መቶ ሺህ ብር በላይ ወጪ ያደረገች ሲሆን 25 ኪሎግራም ዱቄት 5 ሊትር ዘይት ደረቅና ፈሳሽ ሳሙና በቤተሰብ ደረጃ እንዲከፋፈል አድርጋለች ።
በተመሳሳይ አባይ ጓደኛሞች ለፍቅር የተሰኘ የወጣቶች ማህበር በከተማዋ ረዳት ለሌላቸው 15 የአረጋውያን ቤተሰቦች ለእያንዳንዳቸው 35 ኪሎግራም ዱቄት፣ ማጣፈጫ ጥራጥሬና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቀሱ አከፋፍሏል።
የማህበሩ ሊቀመንበር ወጣት ተገኑ አሰፋ እንዳለው 13 አባላት ያሉት ማህበሩ ቀድሞም በበዓላት ወቅት አቅመ ደካሞችን የመጠየቅ ልምድ አለው።
ድጋፍ ከተደረገላቸው አረጋውያን መካከል ወይዘሮ የትናየት ፀሐይ ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል ።በዲላ ከተማ ልባሽ ጨርቅ ንግድ ላይ ተሰማርተው ይሰሩ እንደነበር ተናግረዋል።
በተያያዘ መልኩ የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም በደቡብ ክልል የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የሚውል 760 ሺህ ብር የሚገመት የምግብ ዱቄትና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል ፡፡
ድጋፉን በክልሉ ለተቋቋመው የሀብት አሰባሳቢ ግብረ-ኃይል ያስረከቡት የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አለማየሁ ኃይለጊዮርጊስ እንዳሉት ድጋፉ አቅም የሌላቸው ሰዎችን ከሚደርስባቸው ሁለንተናዊ ጉዳት ለመታደግ የተደረገ ነው ።
በደቡብ ክልል የተቋቋመው የሀብት አሰባሰብ ግብረ-ኃይል ሰብሳቢና የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ እንዳሉት ክልሉ የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመከላከልና አቅም የሌላቸው ወገኖች ለመርዳት ሀብት የማሰባሰብ ስራ እየሰራ ነው።
በክልል፣ በዞን እንዲሁም በከተማና ወረዳ መዋቅሮች እስከ አሁን ከ180 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ የተሰበሰበ ሲሆን 40 ሚሊዮን ብር የሚገመት ቁሳቁስም ከተለያዩ ምንጮች ማግኘት እንደተቻለ ገልጸዋል።
ኮሮና በክልሉ በስፋት ቢከሰት ገቢ የሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ተጎጂ አንዳይሆኑ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ባለሀብቶችና በየደረጃው ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች የበኩላቸውን ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በአማራ ክልል ደግሞ ለቀበሌ ግብርና ባለሙያዎች 2ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የዋጋ ግምት ያላቸው የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ማሰራጨቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አበባው ጌቴ እንደገለፁት የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ለሦስት የከተማ አስተዳደሮችና ለ12 ዞኖች ተሰራጭቷል።
ከተሰራጩት የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች መካከልም 32 ሺህ 400 ባለ130 ሚሊ ሊትር ሳኒታይዘርና ከ21 ሺህ በላይ ፈሳሽ ሳሙና ይገኙበታል።
የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶቹ በገጠር ቀበሌዎች ለሚገኙ 20 ሺህ ለሚጠጉ የቀበሌ ግብርና ባለሙያዎች የሚሰራጭ መሆኑን ገልፀዋል።
የቁሳቁሱ መሰራጨርትም የግብርና ባለሙያዎቹ ከኮሮና ቫይረስ ራሳቸውን በመጠበቅ የግብርና ስራው ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል የሚያግዝ መሆኑን አመልክተዋል።
ለባለሙያዎቹ የተሰራጨው የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ከተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የተገዛ መሆኑ ተጠቁሟል።
በክልሉ ከ3ሺህ 500 በሚበልጡ የገጠር ቀበሌዎች የግብርና ባለሙያዎች ተመድበው አርሶ አደሩን በቅርበት እያገዙት ይገኛሉ ተብሏል ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የማይጨው ችፕ ውድ ፋብሪካና ጉና የንግድ ስራዎች ድርጅት በጋራ ከ549 ሺህ ብር በላይ የሚያወጡ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁሶች ለትግራይ ደቡባዊ ዞን ዛሬ ድጋፍ አድርገዋል ።
የማይጨው ችፕ ውድ ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ አምደፅዮን ሚካኤል በርክክብ ስነ ስርዓት ላይ እንዳሉት ተቋማቱ ድጋፉን ያደረጉት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የዞኑ ህዝብ ለሚያደርገው ጥረት የድርሻቸውን ለመወጣትበማሰብ ነው።
ቫይረሱን አስቀድሞ ለመከላከል ተቋማቱ 13 ሺህ የአፍ መሸፈኛ ጭንብል፣ 1ሺህ 800 ሊትር ሳኒታይዘርና ፈሳሽ ሳሙና ድጋፍ አድርገዋል ።
በቀጣይም ወረርሽኙን ሙሉ በሙሉ እስከሚጠፋ ድረስ ድጋፍቸውን አጠናክሮ እንደሚቀጥሉ ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል ።
በዞኑ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብር ኃይል ፀሓፊ አቶ ሀፍቱ ኪሮስ እንዳሉት ተቋማቱ ያደረጉት ድጋፍ በዞኑ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ያለውን የቁሳቁስ እጥረት የሚያቃልል ነው ።
በሌላ በኩል ደግሞ በጋምቤላ ክልል የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ባለሃበቶች ተሳትፎአቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ጥሪ አቅርበዋል ።
አንድ ባለሃብት የተለገሱትን 15 የሙቀት መለኪያ መሳሪያዎች ለክልሉ ጤና ቢሮ ዛሬ አስረክበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በርክክቡ ወቅት እንደተናገሩት የኮሮና ቫይረስ ሊያስከትል የሚችለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አሸንፎ ለመሻገር የባለሃብቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል።
ቫይረሱ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት መከላከል የሚቻለው ሁሉም ዜጋ የተቻለውን ሁሉ አስተዋፅኦ ማበርካት ሲችል መሆኑን ተናግረዋል።
በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች የተሰማሩት ዲያቆን አይሸሽም ተካ የተባሉት ባለሃብት ያደረጉትን ድጋፍ ከልብ አመስግነው ሌሎች ባለሃብቶችም መሰል ተግባራትን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ካን ጋልዋክ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በድጋፍ የተገኙት የሙቀት መመርመሪያ መሳሪያዎች ክልሉ በዘርፉ የነበረበትን ችግሮች ያቃልላሉ ብለዋል።
በክልሉ ቀደም ሲል የነበሩት የሙቀት መመርመሪያ መሳሪያዎች ስድስት ብቻ እንደነበሩ ጠቁመው አሁን ላይ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ከባለሃብቱ የተገኙትን ጨምሮ የመሳሪዎች ቁጥር ወደ 42 ከፍ ማለቱን ተናግረዋል።
የሶዶ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ደግሞ ከእጅ ንክኪ ነፃ የሆነ የእጅ መታጠቢያ ሰርቶ ለአገልግሎት አብቅቷል ።
የኮሌጁ ዲን ረዳት ፕሮፈሰር ወንድሙ ዳዊት እንደገለጹት ኮሌጁ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የተለያዩ ሙከራዎች ሲያደርግ ቆይቷል።
እስከ አሁን ባደረገው እንቅስቃሴም ከእጅ ንክኪ ነፃ የሆነና በእግር ፔዳል የሚሰራ የእጅ መታጠቢያ መሳሪያ በመስራት ጥቅም ላይ እንዲውል አድርጓል ።
ከቫይረሱ መተላለፊያ መንገዶች አንዱና ዋንኛው ንክኪና የንፅህና ጉድለት በመሆኑ በኮሌጁ የተሰራው መሳሪያ ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት የእጅ ማስታጠቢያውን ለአካባቢው ማህበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል በኮሌጁ የጨርቃ ጨርቅ ዲፓርትመንት በኩል እየተሰራ መሆኑንም ረዳት ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል።
የፈጠራውን ሐሳብ ወደተግባር የቀየሩት በኮሌጁ ሜካኒካል የትምህርት ክፍል መምህር አያሌዉ ዮሐንስ ናቸው።
እሳቸው እንዳሉት የፈጠራ ውጤቱ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የሚደረገውን እንቅስቃሴ በማገዝ በኩል የላቀ አስተዋዕኦ አለው።
የወላይታ ዞን ቴክኒክና ሙያ መምሪያ ኃላፊ አቶ ዳዊት አበበ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እያካሄዱ ያሉት የፈጠራና የምርምር ሥራዎች የሚበረታታ ነው።
በኮሌጁ የተሰራው የፈጠራ ውጤት ለህብረተሰቡ ለማድረስ ከዞኑ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ሃይል ጋር በመተባበር የሚባዛበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ይሰራል ብለዋል።