ህብረተሰቡን ከኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነት ለመከላከል እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ህብረተሰቡን ከኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነት ለመከላከል እየተሰራ ነው
ሚያዝያ 05/2012(ኢዜአ)በተለያዩ አካባቢዎች ህብረተሰቡን ከኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነት ለመከላከል እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።
በሰሜን ሸዋ፣ አዳማ፣ ዲላና ምዕራብ ጎንደር አካባቢዎች ህብረተሰቡን ከኮሮና በሽታ ተጋላጭነት ለመከላከል እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።
በአማራ ክልል የሰሜን ሽዋ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ እንዳለው በትንሳኤ በዓል የግብይት ወቅት ለበሽታው አጋላጭ ባልሆነ አግባብ እንዲከወን እየተሰራ ነው።
ከትንሳኤ በዓል ጋር ተያይዞ ግብይት አካላዊ መራራቅን መሰረት ተደርጎ እንዲፈፀም ትኩረት መስጠታቸውን በመምሪያው የእንስሳትና እንስሳት ተዋጽኦ ግብይት ቡድን ባለሙያ ዶክተር ፈጠነ ሞገስ ለኢዜአ ተናግረዋል።
ለበዓሉ በአካባቢው ብዛት ያላቸው የእርድ እንስሳት ለገበያ እንደሚቀርቡ የሚጠበቅ መሆኑን ጠቅሰው
በዚህ ወቅት ለህብረተሰቡ የበሽታው መከላከያ ምክረ ሃሳቦችን ለመተግበርም ከማስተማር ባለፈ በሁሉም የዞኑ ከተሞች ጊዜያዊ የቁም እንስሳት የግብይት ቦታዎች መመቻቸታቸውን አመልክተዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታሁን ማሞ በበኩላቸዉ የቫይረሱን ስርጭት ስጋት ለመቀነስም ወደ ግብይት ቦታው ለሚገቡ ሰዎች ሁሉ የሰውነት ሙቀት በመለካት የመለየት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ለግብይትና ለሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች ወደ ከተማው ለመጡ ሰባት ሺህ ሰዎች የሙቀት መለካት ስራ መከናወኑንም ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል የአዳማ ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ሳሚራ ሙሐመድ እንደገለጹት አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የወጡ መመሪያዎች ለህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት ተፈፃሚ እየሆነ አይደለም።
ይህም ችግር በተለይ በአዳማ ከተማ በሚገኙ ባንኮች፣ ቴሌና መብራት ኃይል አካባቢዎች እንደሚስተዋል ጠቅሰዋል።
አስተዳደሩ ችግሩን ለማቃለል ከህብረተሰቡ የዕለት ተዕለት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አመራሮች ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
በሌላ በኩል አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ፣ጃንቦ ጆቴና አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ዛሬ በአዳማ ከተማ በመገኘት ለህብረተሰቡ ስለ ኮሮና ቫይረስ ትምህርታዊ ግንዛቤ ሰጥተዋል።
አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በሰጠው አስተያየት “በአሁኑ ወቅት ትብብርና ቅንጅት ከሁሉም በላይ ወሳኝ ነው፤ ባለን እውቀትና ክህሎት ህብረተሰቡን ለማገዝና የድርሻችንን ለመወጣት ጥረት እያደረግን ነው “ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በምዕራብ ጎንደር ዞን ኮሮናን ለመከላከል የተቀመጡ ክልከላዎች እንዲተገበሩ እያስተማሩ መሆናቸውን የኃይማኖት አባቶች ተናገሩ፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የምዕራብ ጎንደር ዞን ሀገረ-ስብከት ስራ አስኪያጅ በኩረ ትጉሃን ዕዝራዳዊት ኃይሉ እንደገለጹት ህዝቡ ከኮሮና ቫይረስ እንዲጠበቅ ቤተክርስቲያኗ አጥብቃ ታስተምራለች።
የእምነቱ ተከታዮች ቫይረሱ እንዳይስፋፋ በጊዜያዊነት በቤታቸው ሆነው አምልኮና ፀሎት እንዲያከናውን በሲኖዶሱ የተላለፈው ውሳኔ እንዲተገበር እየሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በገንዳ ውኃ ከተማ የእስልምና እምነት አባት ሼህ አሊ ሀሰን በበኩላቸው በአካባቢው የህዝቡ የጥንቃቄ መጓደል ለቫይረሱ ሊያጋልጥ የሚችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ህዝበ ሙስሊሙ በመስጊድ ሶላት ሲያደርስ ተገቢውን ጥንቃቄ እንደሚያደርግ አመልክተው ከመስጊድ ውጭ ባሉ ማህበራዊ መስተጋብሮችና እንቅስቃሴዎች ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግ በማስተማር ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ሰራተኞችና የጤና ባለሙያዎች በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ ህብረተሰቡን ለመቀስቀስና ግንዛቤ ለማስጨበጥ የአምስት ኪሎ ሜትር የእግር ጉዞ አካሄደዋል።
የሆስፒታሉ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፍራኦል ንፊታለም በዚህ ወቅት እንዳሉት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ አስተዋጽኦው የጎላ ነው።
በተለይ አካላዊ ርቀትን ከመጠበቅና የተለያዩ የተሳሳቱና ሐሰተኛ መረጃዎችን ከመከላከል አንጸር ተከታታይነት ያለው የማንቃትና የማስገንዘብ ስራ ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል።
“ዩኒቨርስቲው በቀጣይም መሰል የንቅናቄና የግንዛቤ ስራዎች በጌዴኦ ዞንና አጎራባች አከባቢዎች ለማከናውን ዝግጅት አድርጓል “ብለዋል።
በእግር ጉዞው ወቅት “እኛ ለእናንተ በሆሲፒታል ነን እናንተ ሰለእኛ ቤት በመሆን አግዙን፣ የኮሮና ቫይረስ ካልነኩት አይነካም “ የሚሉ መልዕክቶች ተላልፈዋል።