የስኳር ኮርፖሬሽን የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት ያልቻለው በአመራር ብቃት ማነስ ነው ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የስኳር ኮርፖሬሽን የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት ያልቻለው በአመራር ብቃት ማነስ ነው ተባለ
አዲስ አበባ ሰኔ 25/2010 የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ውጤታማ ያልሆነበት ዋናው ምክንያት የአመራር ብቃት ማነስ እንደሆነ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማት ድርጅቶ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ። ቋሚ ኮሚቴው አንዳለው ኮርፖሬሽኑ የሚያጋጥሙትን ችግሮች ተከታትሎ ለመፍታት የሚያስችል የአመራር ብቃት አለመገንባቱ በበጀት ዓመቱ ለምርት መቀነስና ፕሮጀክቶች በጊዜያቸው እንዳይጠናቀቁ ምክንያት ሆኗል። ኮርፖሬሽኑ በበኩሉ የተባሉት እጥረቶችና ችግሮች መኖራቸውን በመግለፅ ኮርፖሬሽኑ ከአቅሙ በላይ የሆነ ኃላፊነት እንዲሸከም መደረጉ ውጤታማነቱ ላይ እክል እንደፈጠረበት አስታውቋል። ኮርፖሬሽኑ የ2010 በጀት የ11 ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርቱን ዛሬ በቋሚ ኮሚቴው ባስገመገመበት ወቅት አንደተገለፀው የስኳር፣ ሞላሰስና ኢታኖል ምርታማነትን በተመለከተ በስኳር ፋብሪካዎች የተመዘገበው አፈፃፀም ከእቅዱ ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ነው። እየተጠናቀቀ ባለው የበጀት ዓመት በሁሉም ስኳር ፋብሪካዎች የተመረተው አገዳ ከእቅዱ ከግማሽ በላይ ማነሱ ለምርቱ መቀነሰ መሰረታዊው ምክንያት ነው ተብሏል። በተጠቀሱት ጊዜያት 353 ሺህ ቶን ስኳር ለማምረት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም ማሳካት የተቻለው ግን 249 ሺህ ቶን ብቻ መሆኑንም ሪፖርቱ ጠቅሷል። ከፕሮጀክቶች ግንባታ ጋር በተያያዘም ተንዳሆ፣ ከሰም፣ ጣና በለስ ቁጥር 1፣ ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1፣ ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2፣ 3 እና 5 በበጀት ዓመቱ በተያዘላቸው እቅድ መሰረት ከ30 በመቶ በታች አፈፃፀም ያሳዩ ናቸው። ቋሚ ኮሚቴው ግን በኮርፖሬሽኑ የተጠቀሱት ችግሮች ቢያጋጥሙም ችግሮቹን በሂደት ለመፍታትና ምርታማነትን ለማሳደግ በየደረጃው ያሉ አመራር አካላት የማስፈፀም አቅም ውሱንነት ዋነኛው ምክንያት ነው ሲል አስገንዝቧል። "በተለይ ለችግሮች ፈጣን ውሳኔ ሰጥቶ ስራዎችን ከማስቀጠል አንፃር የታየ እንዝላልነት አለ" በማለት ነው ቋሚ ኮሚቴው የገለፀው። የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ እንግዳወቅ አብቴ በበኩላቸው የተባሉት እጥረቶችና ችግሮች መኖራቸውን በመግለፅ ኮርፖሬሽኑ ከአቅሙ በላይ የሆነ ኃላፊነት እንዲሸከም መደረጉ ውጤታማነቱ ላይ እክል እንደፈጠረበት ተናግረዋል። በዓመቱ በመንግስት በኩል ሊስተካከሉ የሚችሉ የፀጥታ ችግር፣ የብድር እና የውጪ ምንዛሪ እጥረት እንዳጋጠመም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልፀዋል። ኦሞ ኩራዝ ላይ ባለማቋረጥ እየጣለ ያለው ዝናብ ፋብሪካው ወደ ምርት እንዳይገባ እንቅፋት አንደሆነበትም ዋና ስራ አስፈፃሚው ጠቅሰዋል። በአጠቃላይ ኮርፖሬሽኑ ሲንከባለሉ በመጡ ችግሮች ምክንያት ፕሮጀክቶችን በጊዜ ማሳካት አለመቻሉንና ውል ለማቋረጥና ከአቅም በላይ የሆኑ ችግሮችን በተመለከተ ለቋሚ ኮሚቴውም ሆነ ለበላይ አካላት ጥያቄ ቢያቀርብም መፍትሄ አለማግኘቱን ገልፀዋል። አሁን ላይ አብዛኞቹ ፕሮጀክቶች በተባለው ጊዜ ባለመጠናቀቃቸው ኮርፖሬሽኑን ለተጨማሪ ኪሳራ እየዳረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል። በዚህም ሳቢያ አንዳንድ ፕሮጀክቶችን ሙሉ ለሙሉ አቁሞ ያሉትን ለመፈፀም ኮርፖሬሽኑ ለቦርድ የውሳኔ ሃሳብ ቢያቀርብም ፕሮጀክቶቹን ማቆም "ከግንብ ጋር መጋጨት" መሆኑን እንደገለፁላቸው ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል። ኮርፖሬሽኑ እነዚህና መሰል ተደራራቢ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት አሁን ላይ ከአቅሙ በላይ በመሆኑ መንግስት ተገቢውን ውሳኔ ማስቀመጥ እንዳለበትም ዋና ሥራ አስፈፃሚው ጠይቀዋል። የቀሩ ስራዎችን ለማስቀጠል፣ መቋረጥ ያለባቸውን አቋርጦ ሌሎች የተጀመሩትን ደግሞ አቅም ላላቸው ተቋራጮች መስጠት ያስፈልጋል ሲሉም አሳስበዋል። በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ትልቅ ትኩረት ከተሰጣቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል በ77 ቢሊዮን ብር እየተከናወነ ያለው የስኳር ልማት አንደኛው ነው። አሥር ግዙፍና አዳዲስ የስኳር ፋብሪካዎችን በመገንባት በዓመት ከ4.07 ሚሊዮን ቶን በላይ ስኳር በማምረት ለውጭ ገበያ በማቅረብ በ2007 ዓ.ም መጨረሻ ላይ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት በዕቅድ ተይዞ ነበር።