በኢትዮጵያ በጥጥ እየለማ ያለው መሬት አነስተኛ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ በጥጥ እየለማ ያለው መሬት አነስተኛ መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ ሚያዝያ 29/2010 በኢትዮጵያ ከሦስት ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ለጥጥ ልማት ምቹ ቢሆንም እስካሁን በጥጥ የለማው አነስተኛ መሬት መሆኑን የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡ ለሁለት ቀናት የቆየ የኢትዮጵያ የዘላቂ ጥጥ ልማት ትውውቅ መድረክ በሃዋሳ ከተማ ሲካሄድ የኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ ለኢዜአ እንዳሉት፣ በአገሪቱ እስካሁን በጥጥ እርሻ የለማው መሬት በአጠቃለይ ከ135 ሺህ ሄክታር መሬት አይበልጥም። በዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን መፍታት የሚያስችልና የጥጥ ልማት የሚመራበት ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱንም አቶ ስለሺ ተናግረዋል፡፡ ዘርፉ ኤክስፖርት መር በሆነ የልማት አቅጣጫ ላይ መሰረት ማድረጉን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምርትን ገበያ ላይ ለማቅረብ በዋናነት በግብአትነት ጥቅም ላይ የሚውለው ጥጥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ለጥጥና ለኢንዱስትሪው ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን ለማምረት ምቹ ሁኔታ ያላት መሆኑንም አመልክተዋል ። በኢንስቲትዩቱ የጥጥ ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን አሰፋ በበኩላቸው አገሪቱ ካላት ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት አንጻር ሲታይ ባለፉት 25 ዓመታት በጥጥ የለማው መሬት መጠን አነስተኛ ነው፡፡ በአነስተኛ አርሶ አደሮች የሚለማውንና በባለሀብቶች እጅ ያለውን መሬት በቀላሉ ማልማትና ለጥጥ ምርት የግብይት ስርዓቱን አመቺ ማድረግ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ለጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት በመሰጠቱ የተለያዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተገንብተው ብዙ ባለሀብቶችን ወደሥራ ማስገባት እንደተቻለ የገለጹት ደግሞ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ አቶ ቦጋለ ፈለቀ ናቸው፡፡ ''ለጥጥ ልማት አገሪቱ ያላትን አመቺ የአየር ንብረትና ሰፊ የመሬት ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ኢንዱስትሪዎች ግብዓት ሳይቆራረጥ ማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት እየተደረገ ነው'' ሲሉም ገልጸዋል፡፡ ባለፈው ዓመት በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስተባባሪነት የጥጥ ልማት ዘርፍ የሚመራበት ፍኖተ ካርታ እንዲዘጋጅ መደረጉንም ሚኒስትር ዲኤታው ገልጸዋል። በፍኖተ ካርታው የዘርፉ ማነቆዎች ናቸው ተብለው የሚለዩ ጉዳዮችን ሊፈታ የሚችል ስትራተጂክ አቅጣጫዎች መቀመጣቸውንና በቀጣይ አቅጣጫዎቹን ወደ ተግባር የመቀየር ስራ እንደሚሰራ አመልክተዋል። በኢንስቲትዩቱ የጥጥ ጥራት ምርምርና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ መሰለ መኩሪያ በበኩላቸው በአሁኑ ወቅት በባለሀብቶችና በአነስተኛ አርሶ አደሮች እየለማ ካለው ጥጥ የሚገኘውን የምርት መጠን ለማሳደግ ከወረር ግብርና ምርምር ጋር በጋራ እየተሰራ ነው፡፡ በእዚህም በመስኖ ከሚለማ መሬት በሄክታር ከ2 እስከ 3 ቶን ምርት ፤ በዝናብ ከሚያለማው ደግሞ እስከ 1 ነጥብ 7 ቶን ምርት እንደሚገኝ ጠቁመው፣ ይህን የምርት መጠን በእያንዳንዱ በአማካይ ወደ 3 ቶን ለማሳደግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡ በሃዋሳ በተካሄደው የኢትዮጵያ ዘላቂ ጥጥ ልማት ትውውቅ መድረክ ላይ የቀረቡ ጥናታዊ ጽሁፎች እንደሚያመለክቱት በአሁኑ ወቅት በጥጥ ልማት ከተሸፈነ ማሳ 138 ሺህ ቶን ባለይ ምርት እየተገኘ ነው። በ2025 ዓ.ም ተጨማሪ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በጥጥ በመሸፈን የምርት መጠኑን 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ቶን ለማድረስ ስትራተጂክ ዕቅድ መዘጋጀቱን ለማወቅ ተችሏል።