ቀጥታ፡

የኮሮና ስርጭትን ለመከላከል የቤት ለቤት ግንዛቤ የማስጨበጫ ተግባራት ተጀምረዋል - ጤና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ሚያዚያ 4/2012 (ኢዜአ) የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የቤት ለቤት ግንዛቤ ማስጨበጫ  ተግባራት መጀመራቸውን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።

ሚኒስትሯ በኢትጵጵያ የኮሮናቫይረስ ምላሽ አሰጣጥን በተመለከተ መግለጫ እየሰጡ ነው።

የጤና ሚኒስቴር ዛሬ ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 71 ከፍ ብሏል።  

ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ እንደገለጹት፤ ቫይረሱን ለመከላከል የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል።

ብሄራዊ የጤና ምላሽ ግብረ ኃይል የተቋቋመ መሆኑን ጠቅሰው በጠቅላይ ሚኒስትሩና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ኮሚቴዎች መቋቋማቸውንም ጠቅሰዋል።    

በተለይም ቫይረሱን ለመግታት ቁልፉ ጉዳይ ግንዛቤ በመሆኑ ሚኒስቴሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የኀብረተሰቡን ግንዛቤ ማስፋት ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል።  

አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች የቤት ለቤት ግንዛቤ የማስጨበት ተግባራት ተጀምሯል ያሉት ሚኒስትሯ ይህም በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች እየተካሄደ መሆኑን አብራርተዋል።  

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፤ የጉዞ ታሪክ ያላቸው ዜጎችን በማፈላለግ ከጤና ተቋማት ጋር የማገናኘቱ ተግባርም እየተከናወነ ነው።  

ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችም በተለያዩ ቋንቋዎች ተዘጋጅተው ተደራሽ እየተደረጉ ሲሆን በምልክት ቋንቋም በስፋት ለማቅረብ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ ነው ብለዋል።   

ክልሎች በአሁኑ ወቅት ነጻ የስልክ መስመር መክፈታቸውንም ነው ሚኒስትሯ የተናገሩት።

''በ8335 እና በ952 የሚሰጠውን አገልግሎት ተደራሽነት ለማስፋት ሚኒስቴሩ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር እየሰራ ነው'' ሲሉም ጠቁመዋል።  

ከቫይረሱ ጋር በተገናኘ የሚሰጡ መረጃ አውታሮችን የማስፋት ተግባራት የተከናወነ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ሊያ፤ ዋትስአፕና በሌሎች መተግበሪያዎች መረጃዎች ለማሰራጨት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።   

49 ማኀብረሰብ አቀፍ ሬዲዮኖችን በመጠቀም ግንዛቤ ለማስጨበጥና መረጃዎችን ለማድረስ እየተሰራ እንደሆነም አክለዋል።   

በበሽታው የሚያዙ ሰዎችን በተመለከተ ሚኒስትሯ ለተነሳላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ''ህሙማንን ማግለል ተገቢ አይደለም ማህበረሰቡ አስፈላጊውን እንክብካቤ ሊያደርግላቸው ይገባል'' ሲሉ አብራርተዋል። 

''ነገር ግን ለጥንቃቄ ሲባል የህሙማን አድራሻ ቢገለጽ የሚሉ ጥያዎች ይነሳሉ'' ያሉት ዶክተር ሊያ፤ የታካሚዎችን አድራሻና ተያያዥ መረጃዎች ይፋ ማድረግ የህክምና ሥነ ምግባር እንደማይፈቅድ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም