ቀጥታ፡

ከ15 በላይ የተለያዩ ድርጅቶች፣ ተቋማትና ግለሰቦች ለከተማ አስተዳደሩ የእህል ምርቶችና የቁሳቁስ ድጋፋ አደረጉ

አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 4/2012( ኢዜአ) ከ15 በላይ የተለያዩ ድርጅቶች፣ ተቋማትና ግለሰቦች ለከተማ አስተዳደሩ የእህል ምርቶችን ጨምሮ የተለያዩ የቁሳቁስ ድጋፋ አደረጉ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
 

በመዲናዋ የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ለመከላከል የሚውል ድጋፍ ማበርከት ዛሬም ቀጥሏል።

በዛሬው እለት ከ15 በላይ የተለያዩ ድርጅቶች፣ ተቋማትና ግለሰቦች ለከተማ አስተዳደሩ የእህል ምርቶችን ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶችን በማበርከት ድጋፍ አድርገዋል።

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አርሶ አደሮች 233 ኩንታል ጤፍ፣ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አርሶ አደሮች 130 ኩንታል ጤፍ፣ የየካ ክፍለ ከተማ አርሶ አደሮች 100 ኩንታል ጤፍ ድጋፍ አድርገዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አርሶ አደሮች እና ግብርና ኮሚሽን 150 ኩንታል በቆሎ፣ ለ1ሺህ655 አባወራዎች የጽዳት እቃ እና የምግብ ሸቀጥ አበርክተዋል።

ኦሞቲክ ጀነራል 550 ኪሎ ሙዝ፣ 120 ኩንታል ድንች፣ 120 ኩንታል ሽንኩርትና ቲማቲም፣ አንድ ሺህ የአፍ መሸፈኛ ማስክና 500 ሴፍቲ ጃኬት ሰጥተዋል።

ኮካ ኮላ ካምፓኒ 208 ኩንታል ዱቄት፣ 355 ካርቶን ዘይት፣ 401 እሽግ ፓስታ እና 81 ካርቶን ሳኒታይዘር፣ ከ12 ሺህ በላይ የለስላሳ መጠጥ ድጋፍ አድርጓል።

ጂ እና ኤስ ኢስተር ድራገን 50 ሺህ የአፍ መሸፈኛ ማስክ እና 500 የሜዲካል ልብስ፣ ሳሙኤል ካሳሁን ጠቅላላ አስመጪ አንድ ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የውሃ ማጠራቀሚያ ታንከር አበርክተዋል።

ሀበሻ አስጎብኝና የጉዞ ወኪል 300 ካርቶን ሳሙናና ለህክምና ባለሙዎች ማጓጓዣ የሚሆን ለሁለት ወር የሚቆይ ነጻ አገግሎት እንዲሰጥ አንድ መኪና አበርክቷል።

ኮማ አስመጪና ላኪ ከሰውነት ቢሻው አካዳሚ ጋር በመተባበር 70 ካርቶን የልብስና የገላ ሳሙና፣ 50 ኩንታል ጤፍ ሲያበረክቱ፤ ቶሪያ ሳሙና ፋብሪካ 400 ካርቶን ሳሙና እንዲሁም ሜይላንች ካፌ እና ሬስቶራንት 50 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል።

የአልታድ መንደር ነዋሪዎች 70 ሺህ ብር የሚገመት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የዋልያዎቹና የሉሲዎቹ 120 ሺህ ብር እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን፣ የፕሪሚየር ሊግ እና ሱፐር ሊግ አሰልጣኞች 125 ሺህ ብር ድጋፍ አድርገዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጀነር ታከለ ኡማ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና በማቅረብ ''እየተደረገ ያለው ድጋፋ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል'' ብለዋል።

እነዚህ የድጋፍ እህሎች በመዲናዋ ባሉት 1 ሺህ 200 የሚጠጉ  የምግብ ባንኮች  የሚቀመጡ  ሲሆን በቀጣይ የችግሩ ሁኔታ እየታየ ለአደጋ ተጋላጭ  ለሆኑ ነዋሪዎች  የሚከፋፈል ይሆናል ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም