ቀጥታ፡

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እስካሁን በወጭ ንግዱ ላይ የጎላ ተፅዕኖ አላደረሰም - የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ ሚያዚያ 4/2012(ኢዜአ) የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ እስካሁን በወጭ ንግዱ ላይ የጎላ ተፅዕኖ እንዳላደረሰ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ከውጭ የሚገቡ የፍጆታ ምርቶችን ለመተካት የአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች የምርት መጠንና አይነታቸውን ጨምረው እንዲሰሩ እየተደረገ መሆኑም ታውቋል። 

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የቫይረሱ ወረርሽኝ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለመቀነስ የተለያዩ አማራጭ አሰራሮች እየተተገበሩ ነው።

እስካሁን ባለው ሁኔታ የአገሪቱ ዋና ዋና የወጭ ንግድ ምርቶች በአለም ገበያ ላይ ያላቸው ተፈላጊነት ጤናማ መሆኑን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ኮሮናቫይረስ የሚስፋፋ ከሆነ ጫና ማሳደሩ እንደማይቀርና ለዚህም ከወዲሁ ትኩረት እንደሚያስፈልገውም ጠቁመዋል።

ሚኒስቴሩ ይህንኑ በማስመልከት በአንድ በኩል የወጭ ንግዱ እንዳይጎዳ በሌላ በኩል በአገር ውስጥ የመሰረታዊ ምርቶች እጥረት እንዳይፈጠር እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

እስካሁን ባለው ሁኔታ በተለይም በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ግብይት የሚፈጸምባቸው ምርቶች በዓለም ገበያ ያላቸው የፍላጎት ደረጃ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከዘጠና በመቶ በላይ የቅባት እህሎችን የምትገዛው ቻይና ከበሽታው በማገገም ላይ ስለምትገኝ ፍላጎቷ እየጨመረ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት በአገር ውስጥ ገበያ ላይ ጫና እንዳይፈጥርና ከውጭ የሚገቡ መሰረታዊ ሸቀጦችን ለመተካት ከኢንዱስትሪዎች ጋር በመግባባት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህም ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ከሁለት እስከ አራት ፈረቃዎችን በማውጣት በሙሉ አቅም በመስራት የሚያመርቱትን ምርት አይነትና ብዛት የሚጨምሩበትን ሁኔታዎች እንዲያመቻቹ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ለዚህም ኢንዱስትሪዎችን ከሚደግፉ የፌዴራልና የክልል ተጠሪ ተቋማት ጋር በየሳምንቱ የቪዲዮ ኮንፈረንስ በማካሄድ፣ በአካል በመጎብኘት የሚያጋጥሙ የግብዓት ችግሮችን እንዲፈቱ እየተደረገ ስለመሆኑ አቶ ወንድሙ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም