ቀጥታ፡

ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የምናደርገውን ድጋፍ አጠናክረን እንቀጥላለን...የሃዲያ ዞን ነዋሪዎች

ሆሳዕና፣  ሚያዚያ 4/2012 (ኢዜአ) በኮሮና ቫይረስ ሳይዘናጉ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የሚያደርጉትን ተሳትፎ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሃዲያ ዞን ነዋሪዎች ገለፁ ።

በዞኑ የበሌሞ ወረዳ ሊሳና ቁሳ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አክሊሉ ሱሊቶ በሰጡት አስተያየት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የድርሻቸውን እየተወጡ ነው። 

ከዚህ በፊት 10 ሺህ ብር የሚገመት ሰንጋ ማበርከታቸውን ገልፀው አሁንም  ከኮሮና ቫይረስ እራሳቸውን በመጠበቅ ካለማንም ቀስቃሽ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ ተሳትፎአቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉበት ተናግረዋል ።

በወረዳው የሹርሞ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ሚጊሶ አያኖ በበኩሉ  በወረርሽኙ ሳንዘናጋ ታላቁ የህዳሴ ግድባችንን በማጠናቀቅ ለትውልድ የሚሻገር ታሪካዊ አሻራ ለማኖር በጋራ ልንረባረብ ይገባል ብሏል።

መንግስት በግድቡ ላይ የነበሩት ችግሮችን በመፍታት በቁርጠኝነት ግንባታው እንዲፋጠን አስፈላጊውን ክትትል እና ድጋፍ በማድረግ ላይ ስለሆነ ተጨማሪ ቦንድ ለመግዛት አጋርነቴን አረጋገጣለሁ ሲል ተናግሯል ።

ሌላኛዋ የሆሳዕና ከተማ የሊች አምባ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ወሰንየለሽ አስራት እንዳሉት ደግሞ  ግድቡ ለትውልድ የሚተርፍ ፀጋ በመሆኑ እንደ ዜጋ ቦንድ በመግዛት ተሳታፊ እንደሚሆኑ ገልፀዋል ።

እስከ አሁን የ20 ሺህ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ገልፀው በቀጣይም የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ በሀገር ውስጥና በውጭ ሃገር ያሉ ልጆቻቸውን በማስተባበር ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ አስታውቀዋል፡፡  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም