በሐረሪ ክልል ህብረተሰቡ ኮሮናን ከመከላከል መዘናጋት እንደሌላበት ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል ህብረተሰቡ ኮሮናን ከመከላከል መዘናጋት እንደሌላበት ተመለከተ
ሐረር (ኢዜአ) ሚያዚያ 3 ቀን 2012፡ - በሐረሪ ክልል ህብረተሰቡ እራሱን ከኮሮና ቫይረስን ለመከላከል መዘናጋት እንደሌለበት ተመለከተ።
የክልሉ የኮሮና ቫይረስ መከላከልና ምላሽ ሰጪ ግብረ ኃይል ቫይረሱን ለመከላከል እያከናወናቸው ባሉት ስራዎች ዙሪያ ዛሬ በሐረር ከተማ ተወያይቷል፡፡
በውይይቱ ወቅት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እንደተናገሩት በሽታውን ለመቆጣጠር ግንዛቤን መፍጠር፣የለይቶ ማቆያ ዝግጅትና በሀብት አሰባሰብ በኩል አበረታች ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
በክልሉ በአምስቱም መግቢያና መውጫ ኬላዎች ላይ ሙቀት የመለካት ተግባራት በቀጣይም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በትራንስፖርት እና ገበያ ስፍራዎች ላይ ርቀትን ከመጠበቅ አንጻር አሁንም ቸልተኝነትና የአመለካከት ክፍተት እንደሚስተዋል ርዕሰ መስተዳደሩ ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ እራሱን ከበሽታው ለመጠበቅና ለመከላከል መዘናጋት እንደሌለበት አመልክተው በመንግስት ተቋማት መካከል የቅንጅት ስራ ክፍተት ማስተካከል እንደሚገባም አሳስበዋል።
የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብሳ አብራሂም በበኩላቸው በክልሉ ቫይረሱን ለመከላከል እስከ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ 10ሺህ በራሪ ወረቀቶችን በማዘጋጀት ህዝብ በሚበዛባቸው ዋና ዋና መንገዶች ላይ የመለጠፍ ፣ በጤና ባለሙያዎችና ኃይማኖት አባቶች አማካኝነት የማስተማር ሰራ እየተካሄደ ነው ብለዋል።
ሆኖም አሁንም በህብረተሰቡ ዘንድ ቸልተኝነት ስለሚስተዋል መስተካከል እንዳለበትም አመልክተዋል።
በክልሉ የሚገኙ ባለሀብቶች፣የንግዱ ማህበረሰብና የተለያዩ ተቋማት አቅመ ደካሞችን ለመደገፍ እየተሳተፉ እንደሚገኙ የተናገሩት ደግሞ የክልሉ የሀብት አሰባሰብ አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ አሚና አብዱልከሪም ናቸው።
እስካሁንም ከሁለት ሚሊዮን 500ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።
በተለይ ባለሆቴልና ሆስፒታል ባለቤቶች ድርጅቶቻቸውን ለማቆያ አገልግሎት መስጠታቸውንም ጠቁመዋል።
በውይይት መድረኩ የክልሉ መንግስት ካቢኔ አባላት፣ድጋፍ ሰጪ ተቋማት፣የምስራቅ ሐረርጌ ዞን አመራሮች ተገኝተዋል።