ቀጥታ፡

በገንዳ ውሃ ለይቶ ማቆያ የነበሩ 94 ሰዎች ከኮሮና ከቫይረስ ነጻ በመሆናቸው ወደ ማህበረሰቡ ተቀላቀሉ

መተማ (ኢዜአ ) ሚያዚያ 3/2012  ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በገንዳ ውሃ ለይቶ ማቆያ የነበሩ 94 ሰዎች ከኮሮና ቫይረሱ ነፃ መሆናቸው ተረጋግጦ ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉን የምዕራብ ጎንደር ዞን የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አስታወቀ።


የግብረ-ኃይሉ ምክትል ሰብሳቢና የዞኑ ማህበራዊ ልማት መምሪያ ኃላፊ ሲስተር ክሽን ወልዴ ለኢዜአ  እንደገለፁት  ግለሰቦቹ ላለፉት 15 ቀናት ገንዳ ውሃ ከተማ በተዘጋጀው ለይቶ ማቆያ የነበሩ ናቸው፡፡

እነዚህ ዜጎች በቆይታቸው ጊዜ ምንም ዓይነት የቫይረሱ ምልክት ያላሳዩና  ነፃ መሆናቸው በመረጋገጡ ዛሬ ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

ገንዳ ውሃ ከተማን ጨምሮ በዞኑ ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ የለይቶ ማቆያ ማዕከል መቋቋሙን የጠቀሱት ኃላፊዋ በአሁኑ ወቅት 480 የሚጠጉ ዜጎች በለይቶ ማቆያ እንደሚኖሩም አመልክተዋል፡፡

ከመካከላቸውም ሦስት ግለሰቦች በተደረገላቸው የሙቀት ልኬት መሰረት ከመደበኛው ሙቀት ከፍ ያለና ሌሎች ምልክቶች ያሳዩ በመሆናቸው በመተማ ሆስፒታል በተዘጋጀው የተጠርጣሪ መለያ ውስጥ እንደሚገኙም አስረድተዋል፡፡

የሁለቱ ግለሰቦች የደም ናሙና ለምርመራ ተልኮ ውጤታቸው እየተጠበቀ ነው ያሉት ሲስተር ክሽን

በዞኑ ከሱዳን ጋር በሚያዋስኑ ሁሉም መውጫና መግቢያ ኬላዎች ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም