ቀጥታ፡

በዋግህምራ 250 ኩንታል አልሚ ምግብ ድጋፍ ተደረገ

ሰቆጣ ሚያዚያ 3/2012 በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ለህፃናትና የምግብ እጥረት ላለባቸው ሰዎች የሚውል 250 ኩንታል አልሚ ምግብ ድጋፍ ማድረጉን የኢትዮጵያ እስኩል ማይል ኢንሼቲቭ አስታወቀ። 
በኢንሼቲቩ የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር አስተባባሪ አቶ ዘውዱ አሰገደ ለኢዜአ እንደገለፁት ድጋፉ ከኮሮና መከሰት ጋር ተያይዞ ህፃናት ለከፋ የምግብ አቅርቦት እጥረት ጉዳት እንዳይደርስባቸው ለማገዝ ነው።

የአልሚ ድጋፉ ኮሮና በሀገሪቱ መከሰት ተከትሎ ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ምክንያት እና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ህጻናትና የህብረተሰብ ክፍሎች የሚውል መሆኑን ተናግረዋል።

ከአልሚ ምግቡ መካከል 150 ኩንታሉ ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ምክንያት ህፃናት በቤታቸው ውስጥ እንዲጠቀሙበት የሚያስችል ነው።

ምገባውም በጋዝጊብላ፣ ደሃና፣ አበርገሌ እና ሰቆጣ ዙሪያ በሚገኙ አምስት ትምህርት ቤቶች ለሚገኙ 2500 ህፃናት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።

ቀሪው ደግሞ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ላሉ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲውል ተለይቶ ለብሄረሰብ አስተዳደሩ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ መሰጠቱን ጠቅሰው፤ አልሚ ምግቡም 650 ሺህ ብር ግምት እንዳለው አስረድተዋል፡፡

በኢንሼቲቩ የሰቆጣ አልሚ ምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ  የምግብ እህሎችን በነፃ አዘጋጅቶ ለህብረተሰቡ ለማቅረብ ዝግጁ እንደሆነም አቶ ዘውዱ አመልክተዋል፡፡

የብሄረሰብ አስተዳደሩ የሴቶች እና ህፃናት መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ዝና ጌታቸው በበኩላቸው ድጋፍ በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን የምግብ አቅርቦት ስጋት ለመቀነስ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡

በዚህም  በችግር ውስጥ የሚገኙ አጥቢ እናቶች፣ የኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው ያለባቸው ግለሰቦች ፣ ደጋፊና ረዳት ለሌላቸው  ህፃናት በቅድመያ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ እስኩል ማይል ኢንሼቲቭ በትምህርት ቤቶች ምገባ ከሚያደርገው አስተዋፅኦ በተጨማሪ በብሄረሰብ አስተዳደሩ የኮሮና ወረርሽን ለመከላከል ላደረገው  ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ እስኩል ማይል ኢንሼቲቭ በወይዘሮ ፍሬ አልም ሽባባው አስተባባሪነት " ህፃናት ባሉበት ምግብ ይኑር"  በሚል መርህ  በሃገሪቱ በአምስት ክልሎች የምገባ መርሃ ግብር በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም