የኢጋድ አባል አገራት የገንዘብ ሚኒስቴሮች ለኮሮናቫይረስ የአስቸኳይ ድጋፍ ለማድረግ ወሰኑ - ኢዜአ አማርኛ
የኢጋድ አባል አገራት የገንዘብ ሚኒስቴሮች ለኮሮናቫይረስ የአስቸኳይ ድጋፍ ለማድረግ ወሰኑ
አዲስ አበባ ሚያዝያ 3/2012 (ኢዜአ) የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን /ኢጋድ/ አባል አገራት የገንዘብ ሚኒስቴሮች ለኮቪድ-19 መከላከያ አስቸኳይ ፈንድ ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናገሩ።
የኢጋድ ዋና ፀሃፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከአባል አገር የገንዘብ ሚኒስትሮች ጋር በአውሮፓዊያኑ ሚያዝያ 8 ቀን ስለተካሄደው ሚኒስትሮች እንዲሁም መጋቢት 30 በተደረገው የኢጋድ ጉባዔ መነሻነት ከአባል አገራቱ ሚኒስትሮቹ ጋር የቴሌኮንፈረስ ውይይት አድርገዋል።
በሱዳኑ የገንዘብ ሚኒስትር የተመራው ይኸው ስብሰባ የኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን ዩጋንዳ የገንዘብ ሚኒስትሮች ተሳትፈዋል።
የሱዳኑ ገንዘብ ሚኒስትር በዚህ ወቅት እንዳሉት አገራቸው በኮቪድ-19 ሳቢያ ቀጣናው በምጣኔ ሃብታዊ ድቀት ውስጥ እንዳይገባ ቁርጠኝነቷን ገልጸው፤ ኢጋድም የጉዳዩን ስጋት በቸልተኝነት ሊያየው አይገባም ብለዋል።
ለወረርሽኙ ምላሽ ለመስጠት ተነሳሽነቱን አድንቀው ኮቪድ-19 በቀጣናው የሚያመጣውን ምጣኔ ሃብታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ በአገራት ተናጠል ጥረት ብቻ ሊሳካ ስለማይችል በትብብር መስራትን ይጠይቃል ብለዋል።
የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በበኩላቸው ወረርሽኙ ከ270 ሚሊየን በላይ ለሚሆነው የቀጣናው ነዋሪ ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል ብለዋል።
በመሆኑም ቫይረሱን በፍጥነትና በትብብር መቆጣጠር ይገባል ነው ያሉት።
የአውሮፓ ሕብረት ዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ጁታ ዑርፒሌኔን ሕብረቱ ለአፋጣኝ ሰብዓዊ እርዳታ፣ የጤና ስርዓቱን ማጠናከርና ኢኮኖሚያዊ ቀውስን ለመፍታት ጥረትና ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ሚኒስትሮቹ የኢጋድ ቀጣናዊ የጋራ መከላከል ስትራቴጂ ቀርቦላቸው የተወያዩ ሲሆን ለተግባራዊነቱም ቀጣናዊ የሚኒስትሮች ግብረሃይል ለማቋቋም ተስማምተዋል።
በየአገራቸው ቫይረሱን ለመከላከል ስለሚያደርጉት አገራዊና ዓለም አቀፋዊ የድጋፍ ማሰባሰብ ተሞክሮም ልምድ መለዋጣቸውን ድረጅቱ አስታውቋል።
በበጀት፣ የዋጋ ግመታና ሀብት ማሰባሰብን በተመለከተም በቀጠናው ሰላለው ፍላጎትና ዕዳ ማሰረዝና የገንዘብ ድጋፍ በተመለከተም ተነጋግረዋል።