የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሰጠው መግለጫ - ኢዜአ አማርኛ
የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሰጠው መግለጫ
የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ያደረገውን ስብሰባ አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ
የብልፅግና ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከመጋቢት 30 እስከ ሚያዚያ 2 ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ዓለም አቀፉ የኮሮና ወረርሽኝ በሀገራችን ሕዝቦች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ደኅንነት ላይ ሊያሳርፍ የሚችለውን ተፅዕኖ ለመመከት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ በዝርዝር ሲመክር ቆይቶ የተለየዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
ክቡራትና ክቡራን ኢትዮጵያውያን
ውድ የሀገራችን ሕዝቦች
ፓርቲያችን ሀገራዊ ለውጡን በመምራት ሂደት እያጋጠሙ የነበሩ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የደኅንነት ችግሮችን ለመቅረፍ የተቀናጀና መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ተጨባጭ ውጤቶችን አምጥቷል፡፡ ለውጡ ኢትዮጵያን ፍትሕ የሰፈነባት፣ በዴሞክራሲ የዳበረች፣ በሰብአዊ መብት ጥበቃ የተመሰገነች፣ በኢኮኖሚ የበለጸገች፣ በሰላምና በደኅንነት የተረጋጋች ሀገር ማድረግ መሆኑን በማመን ከዴሞክራሲ ሪፎርሙ ጎን ለጎን የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ጠንካራ የሕግ ማስከበር ተግባራት ለፍሬ በቅተው ከሞላ ጎደል ወደ ሰላማችን ተመልሰናል፡፡
ለሰብአዊ መብትና ለጋራ ተጠቃሚነት ዕንቅፋት የሆኑ ሕጎችና አሠራሮች ተስተካክለዋል። በሁሉም አካባቢዎች ተፈናቅለው የነበሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከሞላ ጎደል ሁሉም ወደ ቀያቸው ተመልሰው የዕለት ተዕለት ኑሮ ጀምረዋል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ሕዝቡን እያማረሩ የነበሩ ታጣቂዎች እና የጎበዝ አለቆችን አደብ ለማስገዛት በተወሰደ ርምጃ ሥርዓት አልበኝነትን ትርጉም ባለው መልኩ መቀነስ ተችሏል፡፡
ኢኮኖሚያችን ከቀውስ ወጥቶ ማንሠራራት ጀምሯል። ሀገራችን ለበርካታ ጊዜ ያካበተችውን መልካም የዲፕሎማሲ ወረት በመጠቀም ከጎረቤት ሀገራት እና ከተቀረው የዓለማችን ክፍል ጋር ያላት ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ግንኙነት ተጠናክሯል። በደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖች መካከል፣ በሱዳን የሽግግር ሂደት እና በኬንያ እና ሶማሊያ መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት የተሠሩ ተግባራት የዲፕሎማሲ ተሰሚነታችንን ያሳደጉ ሆነዋል። ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድን በመከተል በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ብሔራዊ ጥቅማችን ለመጋፋት የሚደረገውን ጥረት ለማክሸፍ በፅናት ታግለናል፡፡ በውጭ የሚኖሩ ዜጎቻችንን መብትና ጥቅም ለማስከበር ተችሏል።
ክቡራትና ክቡራን
በጥቅሉ ወደ አስቸጋሪ ሁኔታ እያመራ የነበረውን ሀገራዊ ሁኔታችንን በማስተካከል፣ ስለ ምርጫ፣ ስለ ሀገራችን ብልፅግና እና ስለ ወደፊቷ ጠንካራ ኢትዮጵያ ማሰብና መስራት በጀመርንበት በዚህ አጓጊ ወቅት በዓለማችን በፍጥነት በመዛመት ሁለንተናዊ ቀውስ እስያስከተለ ያለው የኮሮና ወረርሽኝ በሀገራችንም ተከስቷል።
ቫይረሱ እስካሁን 200 በሚጠጉ ሀገራት ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ አስከትሏል፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን አጥቅቶ ወደ 100 ሺህ ለሚጠጉ ሰዎች ደግሞ የሞት ምክንያት የሆነው ይህ ወረርሽኝ ወደ ሀገራችን ገብቶ 65 ዜጎቻችን ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ተረጋግጧል፡፡
ከነዚህ ውስጥ ለዜጎቻችን ኅልፈተ ሕይወት ምክንያትም ሆኗል፡፡ ነገ ምን ያህል ዜጎቻችንን እንደሚያጠቃ በርግጠኝነት ባናውቅም ሁላችንም ተረባርበን አስከፊ ጉዳት እንዳያስርስብን መዘጋጀትና ችግሩን ለመሻገር ተስፋችንን ለማስቀጠል መረባረብ ይጠበቅብናል፡፡
የተደቀነብንን ፈተና ለማለፍ፣ በሽታውን ለመከላከል፣ ለማከምና ተዛመጅ ጉዳቶቹን ለመቀነስ እንደ ፓርቲም ሆነ እንደ መንግሥት በትኩረት መንቀሳቀስ አለብን፡፡ በዚህ ወቅት ለብልፅግና ፓርቲ ሕዝባችንን ከዚህ ዓለም አቀፋዊ ወረርሽኝ ከመከላከልና ከማዳን የሚበልጥ ተልዕኮ የለም። ፓርቲያችን ከጅምሩ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ለዚሁ ስራ ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ብሔራዊ የወረርሽኝ መከላከል ኮሚቴና ንዑሳን ኮሚቴዎችን በማቋቋም ከላይ እስከታች ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ሀገራዊ ንቅናቄ በመፍጠር እየሰራ ይገኛል፡፡
ከ300ሺህ በላይ የሚሆኑ ከፌዴራል እስከ ቀበሌ ያሉ አመራሮቹን ቀዳሚ ተልእኳቸው ወረርሽኙን የመከላከል ስራ አድርጎ አሰማርቷል፡፡ ወረርሽኙ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ የተወሰዱት እርምጃዎች አበረታች መሆናቸውን የገመገመው ፓርቲያችን የቀጣይ ጊዚያት ዋና ተልእኮና ተግባራችን የኮሮና ወረርሽኝን መከላከል መሆኑን በማመን የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በዝርዝር ጉዳዩች ላይ ተወያይቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፏል፡፡
1ኛ. ከፊትለፊታችን የተደቀናዉን ፈተና በአሸናፊነት ለመወጣትና ሕዝባችንን ከዚህ ዓለም አቀፋዊ ወረርሽኝ መከላከል፤ ማከምና የከፋ ጉዳት ሳያስከትል መቆጣጠር መቻል፤ እንዲሁም ተዛማጅ ጉዳቶቹን ትርጉም በለዉ መልኩ ለመቀነስ፤ በዚህ ወቅት ፓርቲያችን ከዚህ የሚበልጥ ተልዕኮ ያለመኖሩን በመገንዘብ እንደ ፓርቲም ሆነ እንደ መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ እንደለብን ከመግባባት ተደርሷል።
2ኛ. የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ነጻ እና ምቹ ሀገራዊ ሁኔታን ይፈልጋል። በመሆኑም ቫይረሱን ለመቆጣጠር የምንሠራቸው ሥራዎች ከዘላቂ የዴሞክራሲ ግባችንን የማይጣረሱ እንዲሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት በየደረጃው የሚወሰዱ እርምጃዎች ሕግና ሥርዓትን የተከተሉ፣ የጀመርነውን የዴሞክራሲ ጉዞ የማያሰናክሉ፣ ነገር ግን ደግሞ ወረርሽኙ የሚፈልገውን የአስቸኳይ ጊዜ ባሕሪያት የተረዱ መሆን እንዳለባቸው መግባባት ላይ ደርሰናል፡፡
3ኛ. ወረርሽኙን በድንገት እንደታወጀብን ጦርነት በመሆኑ በፍጥነት ጥቃት እያደረሰብን ያለና እንደማንኛውም ጦርነት በኢኮኖሚያችን ላይ የራሱን ከባድ ጫና ሊፈጥርብን ይችላል፡፡ ይሄንን ቫይረስ ለመቆጣጠር የምናደርገው ዘመቻም ሀብታችንንና የሰው ኃይላችንን ስለሚሻማ በኢኮኖሚያችን ላይ ሊፈጥረው የሚችለው ጫና ከፍተኛ እንደሚሆን እንረዳለን፡፡ በመሆኑም የወረርሽኙን ቁጥጥር ሥራችን ኢኮኖሚያችንን በእጅጉ እንዳያናጋና ቀጣይ የብልፅግና ትልማችንን እንዳያደናቅፍ ኢኮኖሚውን ለማነቃቃትና ገበያውን ለማረጋጋት በርካታ ሥራዎችን መሥራት እንዳለብን ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡
4ኛ. የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት በሚደረጉ ርብርቦች መካከል የሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ እንዳይስተጓጎል፣ የኑሮ ውድነት እንዳይጨምርና የዜጎች መሠረታዊ ፍላጎቶች በተቻለ መጠን እንዳይጓደሉ ለማድረግ ከፍተኛ ዝግጁነት ያስፈልጋል፡፡ ወረርሽኙ በዜጎች ሕይወት ላይ የሚያደርሰውን ማኅበራዊ ጉዳት በመንግሥት ዐቅም ብቻ ለመፍታት አይቻልም።
ስለሆነም ከመንግሥት በተጨማሪ ሕዝባችን በዳበረ እርስ በርስ የመረዳዳት ባህሉ ተጋላጭ የሆኑትን ወገኖች እንዲታደግ፤ ማስተባበርና ከዚህ ሀገራዊ ፈተና እንደምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ባቋራጭ ለመክበር የሚፈልጉ ሕገ ወጦችን ከድርጊታቸው ለመግታት ከምንጊዜውም የተለየ የሕግ ቁጥጥር አስፈላጊ እንደሆነ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
5ኛ. በዚህ የወረርሽ ወቅት ብሔራዊ ደኅንነታችን እና ሉአላዊነታችን አደጋ ላይ እንዳይወድቅ አስፈላጊውን ዝግጅት ሁሉ በማድረግ የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም የሚጋፉትን በማናቸውም መንገድ ለመከላከልና አስፈላጊ የሆነውን እርምጃ ሁሉ ለመውሰድ ዝግጁ መሆን እንዳለብን መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
የተከበራችሁ የፓርቲያችን አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች
ፓርቲያችን ለየትኛውም ፈተና የማይበገር፣ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በፅናት ታግሎ ማለፍ የሚችል ፓርቲ ለመሆኑ እናንተ ህያው ምስክሮች ናችሁ፡፡ ዛሬም በኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ የተጋረጠውን ይህን ክፉ ወረርሽኝ መላው ህዝባችንን በማስተባበር በድል አድራጊነት እንደምንወጣው ጥርጥር የለንም፡፡ ስለሆነም በዚህ ፈታኝና አስቸጋሪ ወቅት ቢቻል ጠላት የሆነውን ኮሮና ቫይረስ በማሸነፍ እራሳችንንና ህዝባችንን ለማዳን ካልተቻለ ደግሞ እራሳችንን መስዋዕት በማድረግ ይህን ጠላት ድል በማድረግ ህዝቡን ለማዳን በጋራ እንድንረባረብ ጥሪያችንን እናቀርብላችኋለን፡፡
የተወደዳችሁ የህክምና ባለሙያዎች፤
የተሰማራችሁበት የህክምና ሙያ ለወገናችሁ ፈውስና መድህን አድርጎ አቁሟችኋልና ሁሌም ክብርና ኩራት ይገባችኋል፡፡ ደከመን ሰለቸን ሳትሉ የህብረተሰባችሁን ጤና ለመጠበቅ ላደረጋችሁት ሁሉ ፓርቲያችን በዚህ አጋጣሚ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡ ከወረርሽኙ ጋር የምናደርገው ትግል ከማንም በላይ ዛሬም የናንተን ግንባር ቀደም ተሰላፊነትና ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ነው፡፡ እንደሁልጊዜው በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆናችሁና በፅናት ቆማችሁ ለወገናችሁ ጤና ዘብ እንደምትሆኑ ፅኑ እምነታችን መሆኑን እየገለፅን ወቅቱ በሚጠይቀው የቁርጠኝነት ደረጃ፣ በጀግንነት እንድትረባረቡ ጥሪያችንን እያቀረብን ፓርቲያችን ምንጊዜም ከጎናችሁ መሆኑን ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን፡፡
የተከበራችሁ የፀጥታ አስከባሪ ሃይሎች
ዘመናትን በዋጀ የመስዋእትነት ታሪካችሁ የሀገራችንን ልዕልናና ህልውና ጠብቃችሁ ሰላምና ደህንነትን አጎናፅፋችሁናል፡፡ ዛሬም ከፊታችን የተደቀነው ፈተና የናንተን ቆራጥ ተጋድሎና ጀግንነት ይጠይቃል፡፡ በመሆኑም በተሰማራችሁበት ሁሉ በቆራጥነት በመሳተፍ ሀገራችሁንና ህዝባችሁን ከወቅታዊ አደጋ እንድትታደጉ ፓርቲያችን ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡
የተከበራችሁ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች
ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የሁላችንንም የተባበረና የተቀናጀ ርብርብ ትፈልጋለች፡፡ በመሆኑም የፖለቲካ አመለካከትና ልዩነታችን እንደተጠበቀ ሆኖ ወረርሽኙን ለመከላከል በጋራ እንድንረባረብ ፓርቲያችን ጥሪውን ያቀርብላችኋል፡፡
የተከበራችሁ የሀገራችን የሚዲያና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች
ወረርሽኙን በመከላከል ተግባር በግባር ቀደምትነት ተሰልፋችሁ በየሙያ መስካችሁ ህዝባችንን ለማስተማር፣ ለማሳወቅና ለማስተባበር እያደረጋችሁት ላለው ጥረት ፓርቲያችን አድናቆቱን ይገልጻል፡፡ ወደፊትም ወሳኝ በሆኑት የሙያ መስኮቻችሁ የተዓማኒና የትክክለኛ መረጃ ምንጭ፤ የህብረተሰባችን የግንዛቤ ማሳደጊያ፣ ማስተማሪያና መደጋገፊያ መድረክ ሆናችሁ እንድታገለግሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
ውድ የሀገራችን ሕዝቦች
የኮሮና ወረሽኝ እንደሀገር የሰነቅናቸውን ሕልሞች ሊነጥቀን የመጣ ጠላት ነው። የምናደርገው ጦርነት ኅብረብሔራዊ አንድነቷ የጠነከረ፣ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ያረጋገጠችና ለዜጎቿ ምቹ የሆነች፣ ለኢንቨስትመንት ተመራጭ፣ የምሥራቅ አፍሪካ የቢዝነስና ኢኮኖሚ ማዕከል የሆነች ሀገርን ለመገንባት የሚደረግ የሞት ሽረት ትግል ነው።
ይህንን ትግል አሸንፈን የኢዮጵያን ብልፅግና ማረጋገጥ የዚህ ትውልድ ታሪካዊ ሃላፊነት ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን ወራሪም ሆነ ወረርሽኝ ታግሎን እንጂ አሸንፎን አያወቅምና ዛሬም ይህንን ፈተና በፅናት መክተን የብልፅግና ጉዟችንን እንደምንቀጥል ፓርቲያችን ፅኑ እምነት አለው፡፡ አንድ ሆነን ተጋግዘን እና ተረባርበን አስቸጋሪውን ጉዞ እናልፋለን፤ ወደ ብልፅግና እንሻገራለን፡፡ ስለሆነም መላው የአገራችን ህዝቦች ሁሉንም አቅሞቻችንን አስተባብረን ወረርሽኙን በጋራ እንድንከላከል ፓርቲያችን የከበረ ጥሪውን ያስተላልፍላችኋል፡፡
ሁላችንም ኮሮና ቫይረስን የሚከላከለው ሠራዊት አባላት ነን !!
የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ሚያዚያ 02 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ-አበባ