ቀጥታ፡

የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ተሟልቶ አለመካሄድ በልማት ዕቅዶች ዝግጅት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ ሰኔ 25/2010 በኢትዮጵያ ልደትንና ሞትን ጨምሮ የዜጎች የህይወት ታሪክን የሚመለከቱ ወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ በተሟላ መንገድ ማካሄድ አለመቻሉ በአገሪቱ የልማት ዕቅዶችን ለማዘጋጀት በሚደረገው ጥረት ላይ ተፅእኖ እየፈጠረ መሆኑ ተገለፀ። ይህ የተገለፀው በኩነቶች መረጃ አያያዝ ላይ የሚታየውን ችግር ለመቀነስ የፌዴራል ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ ከሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴርና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ዛሬ በተፈረመበት ወቅት ነው። ልደት፣ ጋብቻ፣ ፍቺ፣ ሞትንና ጉዲፈቻን የተመለከቱ የወሳኝ ኩነት መረጃዎችን በየጊዜው መመዝገብ በአገሪቱ ውጤታማ የልማት ስትራቴጂ ለመቅረፅ እንደሚያስችል ተገልጿል። መንግስት የሚዘረጋቸውን የህግ፣ የአስተዳደርና የማህበራዊ አገልግሎት አቅርቦቶችን ፍትሃዊ ለማድረግና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ መሆኑ ተነግሯል። የኤጀንሲው ቦርድ ሰብሳቢ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቶ ብርሀኑ ፀጋየ እንደተናገሩት፤ ትክክለኛና የተደራጀ የመረጃ አያያዝ ስርዓት አለመኖሩ በአገሪቱ የልማት እድገት እንዳይመጣና ማህበራዊ አገልግሎቶችም እንዲስተጓጎል አድርጎታል። በዚህ ረገድ በተለይ በትምህርትና በጤና አገልግሎት ዘርፍ የወሳኝ ኩነቶች የመረጃ ምዝገባ አስፈላጊነቱ ከፍተኛ በመሆኑ ሁለቱ ተቋማት ከወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ ጋር ለመስራት መዘጋጀታቸውን አድንቀዋል። ስምምነቱ ሴቶችና ህጻናትን የተመለከቱ ወሳኝ ኩነቶች መረጃ ምዝገባ ስርዓትን በአገር አቀፍ ደረጃ ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን የኤጀንሲው የጥናትና ምርምር ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ መኮንን ተናግረዋል። በዚህ መልኩ የሚሰበሰበው መረጃ ሴቶችንና ህጻናትን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ዕቅዶችን ለመንደፍ ከማስቻል ባሻገር መረጃው ለአገራዊ ምጣኔ ኃብትና ማህበራዊ ልማት እንዲሁም ለፍትህ አገልግሎት እንዲውል የሚደረግ መሆኑንም ገልፀዋል። የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስትር ወይዘሮ የዓለም ፀጋዬ በበኩላቸው  ከዚህ በፊት በመረጃ አያያዝ ክፍተት ምክንያት ሴቶችና ህጻናት የተፈለገውን ያህል ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ጠቁመዋል። ''በጋራ ለመስራት የሚያስችለው ስምምነት ሰነድ የተዘጋጀውም ይህን ታሳቢ በማድረግ ነው'' ብለዋል። ስምምነቱ ለትምህርት የደረሱ ህጻናት የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ለማረጋገጥ፣  የትምህርት ግብአቶችና የሰው ኃይል ፍላጎትን በወቅቱ ለማሟላት፣ በዘርፉ የሚስተዋለውን የመረጃ ጥራትና ተዓማኒነት ችግሮችንም ለማቃለል ያስችላል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም