በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ለችግር እንዳይዳረጉ ክትትል እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ለችግር እንዳይዳረጉ ክትትል እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፣ሚያዚያ 2/2012 (ኢዜአ) በተለያዩ የውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ለችግር እንዳይዳረጉ ክትትል እየተደረገ መሆኑን የኢፌዲሪ የውጭ ገዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ለኢዜአ እንዳሉት በተለይ በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በዓለም አቀፉ ደረጃ ከተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ችግሮች ይከሰታሉ።
የተሻሻለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የዜጎችን መብት ለማስከበር ትኩረት መስጠቱን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ በሚፈለገው ደረጃ ባይሆንም በየአገራቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ለዜጎች ድጋፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም ከሳዑዲ አረቢያ በርካታ ዜጎች በየዕለቱ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ መደረጉን በማሳያነት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢተዮጵያዊያን ወደ አገር ቤት ሲገቡም ለ14 ቀናት በለይቶ ማቆያ እንዲጠበቁ ይደረጋል ብለዋል።
አምባሳደር ብርቱካን እንዳሉት ዜጎች ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ችግር እንዳይደርስባቸው ክትትል እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በየአገራቱ ስልላው አጠቃላይ ሁኔታና በመፍትሄው ላይ በቴሌኮንፈረስ በመወያየት ኤምባሲዎች የእርዳታ ጥናት አቅርበው ድጋፍ እንዲደረግ አቅጣጫ መቀመጡን አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በየአገራቱ ያሉ የዳያስፖራ ማህበረሰብ ማህበራት በሽታውን ለመከላከል ለተቋቋመው ኮሚቴ ከሚለግሱት እርዳታ በተጨማሪ ችግር ላይ ለወደቁት ስደተኞችም ደጋፍ እያደረጉ በመሆኑ አመስግነዋል።
በቀጣይም ከሚሲዮኖች ጋር በመሆን ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።