ቀጥታ፡

ምክር ቤቱ ለኮሮናቫይረስ አስቸኳይ ምላሽ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል የብድር ስምምነት አፀደቀ

አዲስ አበባ ሚያዚያ 2/2012(ኢዜአ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር ለኮሮና ቫይረስ አስቸኳይ ምላሽ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል ከ82 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የብድርና እርዳታ ስምምነትን አፀደቀ። 

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 5ተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ተኛ ልዩ ስብሰባው አጀንዳ ካደረጋቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር ለኮሮናቫይረስ አስቸኳይ ምላሽ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የብድር ስምምነት አዋጅ አንዱ ነው።

በዓለም ጤና ድርጅት ዓለም አቀፍ ወረሽኝ የተባለው የኮቪድ-19 በኢትዮጵያ ከመጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ መከሰቱን የጤና ሚኒስቴር ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

የዳበረ የጤና መሰረተ ልማትና ኢኮኖሚ በሌላቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ወረሽኙ የሚያደርሰው ጥፋት የከፋ መሆኑ በባለሙያዎች ሲገለጽ ቆይቷል።

በመሆኑም የወረርሽኙን የጉዳት መጠን ለመቀነስ የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር ለኮሮናቫይረስ አስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል 41 ነጥብ 3 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በእርዳታ መልክ እና 41 ነጥብ 3 ሚሊዮን ደግሞ የብድር ፕሮጀክት መቀረፁን መንግስት አስታውቋል።

መንግስት ከተለመደው አሰራር በተለየ መልኩ በአፋጣኝ የተቀረፀ እንደሆነ የገለጸው ፤ይህ ፕሮጀክት በጤና ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አማካኝነተ ለሚቀጥሉት 15 ወራት እንደሚተገበር አስታውቋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በፕሮጀክቱ ሊተገበሩ የታቀዱ ዋና ዋና ተግባራትን ዘርዝረዋል።

የመድኃኒትና የሕክምና መሳሪያዎች አቅርቦት፣ የጤናው ዘርፍ ዝግጁነት አቅም ግንባታ ስልጠና ፣ የማህበረሰብ ውይይቶችና መረጃ ማድረስ እና በቫይረሱ የተያዙትን በልይቶ ማቆያ የማቆየት ተግባራትን ለመፈፀም ያለመ ፕሮጀክት መሆኑንም ተናግረዋል።

አጠቃላይ የፕሮጀክቱ ወጪ 82 ሚሊዮን 600 ሺህ የአሜሪካን ዶላር መሆኑን አስረድተው 50 በመቶ በብድር ቀሪው 50 በመቶ ደግሞ በእርዳታ የሚገኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ምክር ቤቱ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ከመረመረ በኋላ አዋጅ ቁጥር 1190/2012 አድርጎ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።

በተያያዘ ዜና በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ የሚውሉ 2 የብድር ስምምነት አዋጆችን ምክር ቤቱ አጽድቋል።

የመጀመሪያው በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለሁለተኛው የእድገትና ተወዳዳሪነት የልማት ማስፈፀሚያ የተደረገው የብድር ስምምነት አዋጅ ነው።

ይህም ከዓለም ባንክ የተገኘውን 187 ነጥብ 80 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ብድር ምክር ቤቱ ያፀደቀ ሲሆን መንግስት እየወሰደ ያለውን የፖሊሲ እርምጃዎች ለመደገፍ እንዲቻል እና የፌዴራል መንግስት የ2012 ዓ.ም በጀት በተሟላ ሁኔታ ፋይናንስ ለማድረግ የሚውል መሆኑ ተገልጿል።

ሌላኛው ደግሞ በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠርና መከላከያ ማዕከል ክፍለ አህጉራዊ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የብድር ስምምነት ነው።

ለዚህ ማስፈፀሚያ የሚውል 150 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ምክር ቤቱ ያፀደቀ ሲሆን 75 ሚሊዮኑ ዶላሩ በእርዳታ ቀሪው 75 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ በብድር መልክ የተገኘ መሆኑ ተመልክቷል።

ምክር ቤቱ ይሄንን የብድር ስምምነት በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም