ቀጥታ፡

የአማራ ክልል ምክርቤት እና ኮካኮላ ካምፓኒ ለኮሮና መከላከል ድጋፍ አደረጉ

ሚያዝያ 2/2012(ኢዜአ) የአማራ ክልል ምክር ቤት እና የኮካኮላ ካምፓኒ ለኮሮና ቫይረስ ለመከላከል የሚያግዝ የገንዘብና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ እንደገለጹት ምክር ቤቱ የህዝብን አደራ ለመወጣት ከበጀቱ በመቀነስ ግማሽ ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉን ለህይዎታቸው ሳይሳሱ በሽታውን በመከላከል ግንባር ቀደም ለሆኑ የህክምና ባለሙያዎች አልባሳት የሚውል ነው።

ቫይረሱን ለመከላከል የህክምና ባለሙያዎቹ የተሟላ አልባሳት የሌላቸው በመሆኑ እጥረቱ እንዲሟላ ለማገዝ  እንደሆነም ተናግረዋል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመከላከያ ገዎንና የፊት መሸፈኛ ማስክ አምርቶ እንዲያቀርብም ድጋፉ ለዩኒቨርስቲው መሰጠቱንም አመልክተዋል።

ምክር ቤቱ በየደራጀው ህዝብን በማስተባበር የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በሽታውን ለመከላከል  ባለሃብቶች፣ ድርጀቶችና አቅም ያላቸው ግለሰቦች ድጋፍ እንዲያደርጉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ሰብሳቢ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ በበኩላቸው የክልሉ ምክር ቤት የህክምና ባለሙያዎች ደህንነታቸውን ለመጠበቅ  ድጋፍ ማድረጉ የሚያስመግነው  መሆኑን ተናግረዋል።

"ምክር ቤቱ እስከ ቀበሌ ተደራሽ በመሆኑ የጤና ባለሙያዎችና የመንግስት አካላት የሚሰጧቸውን መመሪያዎች ህብረተሰቡ ተግባራዊ እንዲያደርግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን መስራት ይጠበቅበታል "ብለዋል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለህክምና ባለሙያዎች አግልግሎት የሚውል አልባሳት ማምረት መጀመሩን የተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶከተር ፍሬው ተገኘ ናቸው።

አልባሳቶቹ ተመርተው የሚሰራጩት በነፃ መሆኑን ጠቅሰው፤ "ምክር ቤቱ ያደረገው ድጋፍ የአልባሳቱን መስሪያ ቁሳቁስ ለመግዛት የሚውል ነው" ብለዋል።

አልባሳቱን በፍጥነትና በብዛት ጥራታቸውን ጠብቆ በማምረት ለህክምና ባለሙያዎች እንዲደርሱ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ በኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ሼር ካምፓኒ የባህር ዳር የምርት ክፍል ኃላፊ አቶ ኤባ መላኩ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል እንዲቻል 700 ሺህ ብር ግምት ያላቸው ቁሳቁሶች ድጋፍ  ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

420 ካርቶች ፓስታ፣ ማካሮኒና ሩዝ፣ 42 ካርቶን የምግብ ዘይትና 500 ሊትር ሳኒታይዘር ከድጋፉ መካከል ይገኙበታል።

ድጋፉን ለባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ዛሬ ማስረከባቸውን ጠቅሰው  በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ  እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

በርክክቡ ስነስርዓት ወቅት  የከተማው አስተዳደር  ምክትል ከንቲባ አቶ አማረ አለሙ እንዳሉት ለበሽታው መከላከል ከባለሃብቱ፣ ድርጅቶችና ግለሰቦች እስካሁን አምስት ሚሊዮን ብር ማሰባሰብ ተችሏል።

የኮካ ኮላ ካምፓኒ  ያደረገው ድጋፍ የሚያስመሰግነው መሆኑን ጠቅሰው፤ ሌሎች ካምፓኒዎችም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅረበዋል።

የክልሉ መንግስት ቫይረሱን ለመከላከል 150 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ቀደም ሲል ዘግበናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም