ቀጥታ፡

ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ ለመላክ ፈቃድ የተሰጣቸው ድርጅቶች በአገር ውስጥ ሲሸጡ በዝምታ መታለፍ የለባቸውም ተባለ

አሲስ አበባ ሰኔ 25/2010 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶችን ወደ ውጭ ለመላክ ፈቃድ የተሰጣቸው ድርጅቶች በአገር ውስጥ ሲሸጡ በዝምታ መታለፍ የለባቸውም አለ። አገሪቱ በ2010 በጀት ዓመት ከዘርፉ 237 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ብታቅድም ማሳካት የቻለችው ከ120 ሚሊዮን ዶላር እንደማይበልጥ የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት መረጃ ያሳያል። የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን የእቅድ ዘመን መረጃ እንደሚያሳየው በ2011 ዓ.ም ከዘርፉ 556 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ቢታለምም የኢንስቲትዩቱ የ2011 በጀት ዓመት እቅድ ግን ካለፈው ዓመት ጋር ተመሳሳይ ነው። ለዚህ ዝቅተኛ የእቅድ አፈፀፀም ደግሞ የገበያ ትስስር አለመፈጠር፣ ድርጅቶች ምርታቸውን ወደ ውጭ ለመላክ ቢስማሙም በአገር ውስጥ ገበያ ላይ ማተኮር፣ የኢንዱስትሪ ግብዓቶች በብዛት ከውጭ ማስገባት በዋናነት ተጠቅሰዋል። በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ መኩዬ እንዳሉት" የአገሪቱን የወጪ ንግድ ለማሳለጥ ፈቃድ የተሰጣቸው ድርጅቶች ሚናቸውን በአግባቡ እንዲተገብሩ መከታተል ይገባል።" ለዚህም ኢንስቲትዩቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት በጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ የተሰማሩ ፋብሪካዎችን መቆጣጠርና መከታተል ይኖርበታል ብለዋል። ኢንስቲትዩቱ አላሰራ ያሉት ደንቦችና መመሪያዎች ካሉ ወይም የተሻለ አሰራር ማውጣት ካስፈለገ ችግሮችን በጥናት ተመስርቶ ለሚመለከተው አካል ማቅረብ ይኖርበታል ነው ያሉት። የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶችን ወደ ውጭ ለመላክ ፈቃድ የተሰጣቸው ድርጅቶች በአገር ውስጥ ሲሸጡ በዝምታ መታለፍ የለባቸውም ብለዋል። የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በበኩሉ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማስተካከል በጥናት የተለዩ አሰራሮችን ብናወጣም የሚቀበለን አጥተን በአግባቡ መቆጣጠር አልቻልንም ብሏል። የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ እንዳሉት፤ በወጪ ንግድ ላይ እንዲሰማሩ ፈቃድ የተሰጣቸው ድርጅቶች ከሚናቸው ውጭ ሲገኙ መቆጣጠር የሚያስችል መመሪያ ወጥቷል። ነገር ግን በዘርፉ ባለድርሻ አካላት መካከል "አንዱ ሰጭ ሌላው ነሺ" እየሆነ አሰራሩ ባለመተግበሩ ከተሰጣቸው መመሪያ ውጭ የሚሰሩ ድርጅቶችን በአግባቡ መቆጣጠር አልቻልንም ብለዋል። አንዳንድ ድርጅቶች ምርታቸውን ሆን ብለው በማበላሸት ለአገር ውስጥ ገበያ እንዲውል እያደረጉ ስላስቸገሩን ማንኛውም ፋብሪካ ያመረተው ምርት ጥራቱ ለውጭ ንግድ የማይመጥን ከሆነ ለአገር ውስጥ ገበያ እንዳያቀርብ የሚል መመሪያ ብናወጣም ሰሚ አላገኘንም ነው ያሉት። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራና በየወሩ የሚካሄድ "የኤክስፖርት ማስተባበሪያ ኮሚቴ" ችግሮችን ለመወያየት መልካም አጋጣሚ ፈጥሮ እንደነበር የገለጹት አቶ ስለሺ ውይይቱ ከተቋረጠ ወራት መቆጠሩን አስታውቀዋል። የኤሌክትሪክ መቆራረጥ፣ የብድር ስርዓቱ ቢሮክራሲ፣ ለባለሃብቶች በቂ የማበረታቻ ስርዓት አለመኖሩ የወጪ ንግዱ ፈተናዎች በመሆናቸው ተቀራርበን ልንሰራ ይገባልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም