የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እየሰራ ነው

60

ጋምቤላ፤  ሚያዚያ 1/2012(ኢዜአ) የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ሚና ለመወጣት እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ኡጁሉ ኡኮክ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት የኮሮና ቫይረስ ሊያስከትል የሚችለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ለመከላከል ዩኒቨርሲቲው በክልሉ ከተቋቋመው ግብረ ኃይል ጋር በቅንጅት እየሰራ ነው።

የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ መግባቱ ከተሰማ ጊዜ ጀምሮ ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎቹን ፣ ሰራተኞቹንና የአካባቢውን ማህበረሰብ ከችግሩ ለመታደግ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱንም ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው ለኮሮና ቫይረስ ለይቶ ማቆያና የህክምና አገልግሎት መስጫ የሚውሉ እያንዳንዳቸው አራት ወለል ያላቸው ሶስት ህንፃዎች ዝግጁ አድርጓል ።

የክልሉ ማህበረሰብ ስለ ቫይረሱ ያለው ግንዛቤ ውስን መሆኑን በመገንዘብም ጋምቤላ ከተማን ጨምሮ በሁሉም ወረዳዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርትና የቅስቀሳ ዘመቻ ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ለአካባቢው ማህበረሰብ የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር አምርቶ ለማሰራጨት አስፈላጊው የጥሬ እቃ ግብዓት መገዛቱን የጠቆሙት ፕሬዘዳንቱ የማምረት ስራው በዚህ ሳምንት እንደሚጀመር አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም