ቀጥታ፡

የመንግስት ልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅትን ገመገመ

አዲስ አበባ ሰኔ 25/2010 በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ውጤታማ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገመገመ። ቋሚ ኮሚቴው የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ሶስት የአገልግሎት ተቋማትን ሰኔ 12 እና ሰኔ 23 ቀን 2010ዓ.ም ለሁለት ቀናት ጎብኝቷል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ገብረእግዚአብሔር አርኣያ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ቋሚ ኮሚቴው የጎበኛቸው የድርጅቱ ተቋማት የቃሊቲ ደረቅ ወደብ፣ ቢሸፍቱ የሚገኘውን የባቦጋያ ማሪታይም ማሰልጠኛ ተቋምና የሞጆ ደረቅ ወድብና ተርሚናል ናቸው። በዚህም "ተቋሙ ከነበረበት ውስብስብ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለወጠ መሆኑን ተገንዝበናል" ብለዋል። የሞጆ ደረቅ ወደብና ተርሚናል አገልግሎት የዘረጋቸው ዘመናዊ አሰራሮች ለአብነት ያነሱት አቶ ገብረእግዚአብሔር፤ ሰፊ የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር የተፈጠረበትና የአገልግሎት አሰጣጥ ፍጥነቱን ያሳደገበት አጋጣሚ ነው ብለዋል። በተለይም ድርጅቱ ከሰሞኑ ያሰመረቀው የዘመናዊ የተሽከርካሪዎች የበር ላይ መቆጣጠሪያና የባቡር ላይ ጭነት መጫኛና ማራገፊያ ቴክኖሎጂዎችን ቋሚ ኮሚቴው አድንቋል። የድርጅቱ አካሄድ ለወጪ ንግዱ ፈጣን ምላሽ ከመስጠት ባለፈ "ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው፤ የመልቲ ሞዳል ስርዓቱን ይበልጥ ውጤታማ የሚያደርግ አሰራር ተከትሎ እየሄደ ነው"  ነው ያሉት። ያም ሆኖ ተቋሙ በኤሌክትሪክ ኃይልና በውጭ ምንዛሬ እጥረት የሚፈለገውን ስራ እንዳያከናውን እንቅፋት የሆነበት ጉዳይ እንዳለ አንስተዋል። በማሪታይም ሰልጣኞች ረገድም ሰልጥነው የወጡ የባህር ላይ ሰራተኞች በተገቢው መልኩ የስራ ግንኙነት መፈጠር እንዳለበት ተናግረዋል። በሌላ በኩል በቃሊቲ ደረቅ ወደብ መወገድ ያለባቸው በርካታ ንብረቶች እንዳሉ ገልጸው፤ የሚወገዱት በካይዘን አሰራር ተለይተው እንዲወገዱ፤ ጥቅም ላይ የሚውሉትም ጥቅም ላይ እንዲውሉ በፍጥነት እንዲሰራ ከድርጅቱ አመራሮች ጋር ቋሚ ኮሚቴው መነጋገሩን ገልጸዋል። በድርጅቱ የወደብና ተርሚናል አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ደሳለኝ ጉቱ በበኩላቸው የቋሚ ኮሚቴውን ግምገማ በመቀበል ድርጅቱ የጀመራቸውን ዘመናዊ አሰራሮች በሁሉም ደረቅ ወደቦች ለማስፋት እንደሚሰራ ገልጸዋል። በቃሊቲ የደረቅ ወደብ ለረጂም ጊዜ የቆዩ ኮንቴይነሮች ጉዳይ የድርጅቱ ኃላፊነት የማሳወቅ ስራ እንደሆነ ገልጸው፤ ከጉምሩክ ባለስልጣን ጋር በመተባበር ኮንቴይነሮች እንዲነሱ የማድረግ ስራዎችን እንደሚያከናውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም