የከተማ አስተዳደሩ ለቤት አከራዮች ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ በርካቶች ምላሽ እያሳዩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የከተማ አስተዳደሩ ለቤት አከራዮች ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ በርካቶች ምላሽ እያሳዩ ነው

አዲስ አበባ መጋቢት 30/2012 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለቤት አከራዮች ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ በርካቶች ተከራዮቻቸው ለተወሰነ ወራት በነጻ እንዲጠቀሙ እያደረጉ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ዛሬ ጠዋት የቤት ባለቤቶች ለተከራዮቻቸው ለተወሰነ ጊዜ ወርሃዊ ክፍያ እንዲተዉላቸው ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ይህን ጥሪ ተከትሎም በመዲናዋ የሚገኙ የመኖሪያ ቤት፣ የድርጅቶችና የመጋዘን አከራዮች ከአንድ እስከ ሦስት ወር የኪራይ ክፍያ በመልቀቅ በነጻ እንዲገለገሉበት እያደረጉ ነው።
ከነዚህ መካከል በአቃቂ ቃሊቲ አካባቢ የሚኖሩት አቶ ለማ ታደሰ ለ19 የቤት ተከራዮቻቸው ለሦስት ወር በነጻ እንዲጠቀሙ ፈቅደዋል።
ሰባራ ባቡር አካባቢ የሚገኘው የእድገት በህብረት ሕንጻ ባለቤት አቶ ዘሩ ገብረሊባኖስ 150 ለሚሆኑ ተከራዮቻቸው ለሁለት ወር በነጻ እንዲጠቀሙ ፈቅደዋል።
እድገት በህብረት ለራሱ ድርጅት ሠራተኞችም ለአንድ ወር ተጨማሪ ክፍያ መስጠቱ ተመልክቷል።
በቦሌ ከፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዘማሪያም ደበሌ በበኩላቸው ከስድስት ተከራዮቻቸው የአንድ ወር ክፍያ እንደማይቀበሉ ገልጸዋል።
ለ360 ሠራተኞቻቸው ለሦስት ወር ክፍያ በመክፈል ከቤት እንዲውሉ ያደረጉት ደግሞ የሰይድና ሃና ጋርመንት ባለቤት አቶ ሰይድ ሀሰን የተባሉ ግለሰብ ናቸው።
አቶ ጌታቸው ተስፋ የተባሉ ግለሰብም በተመሳሳይ በድርጅቱ ለሚሰሩ 347 ሠራተኞች የወር ደመወዝ በመክፈል ሠራተኞች እቤት እንዲወሉ ማድረጋቸው ተገልጿል።
ሌሎች በርካታ ግለሰቦችም በተመሳሳይ መልኩ ለቤት ተከራዮቻቸው ከአንድ እስከ ሦስት ወር የኪራይ ክፍያ በመልቀቅ በነጻ እንዲጠቀሙ እያደረጉ መሆናቸው ነው የተገለጸው።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በዚህ ወቅት የኮሮናቫይረስ መከሰት ካስከተላቸው ችግሮች መካከል አንዱ የንግድ ሥራዎች እንዲቀዛቀዙ ማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህን ተገንዘበው የቤት አከራዮች ከጅምሩ እየሰጡት ላለው ቀና ምላሽ ምስጋና በማቅረብ ያለው መረዳዳት እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
በተያያዘ ዜና ከተማ አስተዳደሩ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል እያከናወነ ላለው የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራ በዛሬው እለት ብቻ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ የገንዝብ ድጋፋ ተደርጓል።
ዛሬ ድጋፍ ካደረጉ አካላት መካከል የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሠራተኞች ከደመወዛቸው ላይ በማዋጣት ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ለግሰዋል።
እንዲሁም ራይድ ድርጅትና አሽከርካሪዎቹ 1 ሚሊዮን 30 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።
መካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን 1 ሚሊዮን ብር እና 'ክራይስት አርሚ' የተሰኘ ቤተክርስቲያን በተመሳሳይ 1 ሚሊዮን ብር ለግሰዋል።
ሌሎች ድርጅቶችም ከተማ አስተዳደሩ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል እየሰራ ላለው ሥራ የሚውል የተለያየ መጠን ያለው የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።