የስልጤ ዞን ነዋሪዎች ደም ለገሱ - ኢዜአ አማርኛ
የስልጤ ዞን ነዋሪዎች ደም ለገሱ
ወራቤ ሰኔ 25/2010 የስልጤ ዞን ነዋሪዎች በአዲስ አበባ በተካሄደ የድጋፍ ሰልፍ ላይ በተፈፀመ የቦምብ ጥቃት ለተጎዱ ዜጎች ደም ለገሱ። በደም ልገሳው የዞኑ ሁሉም ወረዳና የከተማ አስተዳደር ነዋሪዎችን የተሳተፉ ሲሆን ዶክተር አብይ ያመጧቸውን ፈጣን ለውጦች በመደገፍም የድጋፍ ሰልፍ አካሂደዋል። ነዋሪዎቹ በመስቀል አደባባዩ የድጋፍ ሰልፍ ላይ በወጡ ዜጎች የተፈጸመው ጥቃት እንዳሳዘናቸውና አደጋ አድራሾችን እንደሚያወግዙ ገልጸዋል። አደጋ የደረሰባቸውን ወገኖች ለመደገፍ በፈቃደኝነት ደም ለመለገስ መወሰናቸውንና ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብም የደም ልገሳው ተሳታፊ እንዲሆን ሃሳብ አቅርበዋል። ደም ከለገሱት ነዋሪዎች መካከል አብዱል ሃኪም ተሚም እንደተናገረው በደረሰው የቦንብ ፍንዳታ በደረሰው ጉዳት እንዳዘነና የወገኑን ደም ለመተካት የደም መለገሱ ፕሮግራም ላይ ተገኝቶ ደም መለገሱን ተናግሯል ሌላው ነዋሪ አብዱልሰመድ አብደላ በበኩሉ ደም መለገስን የመሰለ ስጦታ የሌለ መሆኑን ጠቅሶ ደም ከማፈሰስ ደም መለገስ የሚለውን መሪ ቃል ተከትሎ ደም የለገስ መሆኑን አስታውቋል ፡፡ ደም በመለገሱ ፕሮግራም በመሳተፉ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማውና የለውጡ ተደማሪ በመሆን ደሙን እንደለገሰ የተናገረው ደግሞ የስልጤ ዞን ነዋሪ ዘሃያቱ ሙክታር ነው ፡፡ ነዋሪዎች የደም ልገሳው ምንም እንኳን በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች የታሰበ ቢሆንም በተለያየ ህመም ምክንያት ደም የሚያስፈልጋቸው ወገኖችን ለመርዳት ድጋፉ ቀጣይነት እንደሚኖረው አረጋግጠዋል። ሁሉም ዜጋ በአገሪቱ እየታዩ ያሉ ለውጦችን በመደገፍ አንድ ኢትዮጵያን ለመፍጠር መረባረብ እንዳለበትም ነዋሪዎቹ በደም ልገሳ ወቅት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ ለተመዘገቡ ለውጦች ድጋፍና ዕውቅና ለመስጠት ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም በተጠራ ሰልፍ ላይ በተፈፀመ የቦምብ ጥቃት በሰው ህይወት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል።