ለአካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን የ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር እና የ183 ተሽከርካሪ ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ለአካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን የ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር እና የ183 ተሽከርካሪ ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ መጋቢት 28/2012(ኢዜአ) የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተለያዩ ማህበራትን በማስተባበር ለአካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን የ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብርና 183 የአካል ጉዳተኛ ተሽከርካሪ ድጋፍ አደረገ።
የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተለያዩ ማህበራትን በማስተባበር ለአካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን የ3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብርና 183 የአካል ጉዳተኛ ተሽከርካሪ ድጋፍ አደረገ።
ድጋፉ አካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን ለኮሮናቫይረስ ያላቸውን ተጋላጭነት ለመቀነስ ያለመ መሆኑም ተመልክቷል።
የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ ድጋፉ በተደረገበት ወቅት እንዳሉት፤ አካል ጉዳተኞችና አረጋዊያን ከሌላው በበለጠ ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተጋላጭ ናቸው።
"አካል ጉዳተኞች የሚጠቀሟቸው የአካል ድጋፍ መሳሪያዎች በአግባቡ የማይያዙ መሆናቸውና አረጋዊያኑም ብዙዎቹ የሰውን ድጋፍ ስለሚፈልጉ ተጋላጭነታቸው ይሰፋል" ብለዋል።
ዶክተር ኤርጎጌ እንዳሉት፤ ሚኒስቴሩ ከአረጋዊያንና አካል ጉዳተኞች ማህበራት ጋር የሚያደርገውን ድጋፍ በመላ አገሪቱ ተደራሽ ለማድረግ ይሰራል።
ማህበራቱ ድጋፉን ከተለያዩ ለጋሾች እንዳገኙ የጠቆሙት ሚኒስትሯ፤ ይህንንም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል እንዲውል በጋራ ስምምነት ላይ መደረሱን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ አረጋዊያንና ጡረተኞች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ክፍሉ ድጋፉ ለሌላው ማሳያ እንደሚሆን ገልጸው፤ አረጋዊያን የሚገጥማቸውን ችግር ለመቋቋም ህዝቡ እንዲተባበር ጠይቀዋል።
ብሔራዊ የአካል ጉዳተኞች ማህበር ሊቀመንበር አቶ አባይነህ ጉጆ በበኩላቸው ለአካል ጉዳተኞች ትብብር ያስፈለገው የአካል ጉዳተኞቹ የሚጠቀሟቸው ቁሶች ውድ በመሆናቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ከገንዘብ ድጋፉ 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን የሚሆነው ለኢትዮጵያ አረጋዊያንና ጡረተኞች ማህበር፣ 300 ሺህ ለኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበር እንዲሁም 651 ሺህ 474 ብር ለኢትዮጵያ አረጋዊያን ብሔራዊ ማህበር እንዲሰጥ ተደርጓል።
በአይነት ከአጋፔ ግብረ ሰናይ ድርጅት የተገኙትን 183 የአካል ጉዳተኛ ተሽከርካሪዎች ጨምሮ የንጽህና መጠበቂያ ደረቅና ፈሳሽ ሳሙናዎችን ለማህበራቱ አስረክቧል።
በቀጣይም ድጋፎቹ በማህበራቱ በኩል አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ይሆናሉ ተብሏል።
በኢትዮጵያ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ የሚሹ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን አካል ጉዳተኞች እንዲሁም 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን አረጋዊያን እንዳሉ ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያሳያል።