ቀጥታ፡

በሁለት ዞኖች ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 378 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወሰደ

ሆሳዕና  መጋቢት 28/2012 (ኢዜአ) በሃድያና በከንባታ ጠምባሮ ዞኖች ወቅታዊ ጉዳይን ሽፋን በማድረግ በሸቀጦች  ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ 378 የንግድ ተቋማት ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰዳቸውን የዞኖቹ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያዎች ገለጹ።

የሃድያ ዞን ንግድና ገቢያ ልማት መምሪያ ኃላፊ ዶክተር ኢዮብ በቀለ እንዳሉት በሀገሪቱ  የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ምክንያት በማድረግ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 208 ነጋዴዎች በግብረ ኃይል የክትትል ስራ ተደርሶባቸዋል ። 

ነጋዴዎቹ የአቅርቦት ችግር በሌላቸው ምርቶች ላይ ያለ በቂ ምክንያት የመሸጫ ዋጋ ዝርዝር ሳይለጥፉ በከፍተኛ ዋጋ ሲሸጡ በግብረ ኃይሉ ድንገተኛ ፍተሻ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል ። 

ከተያዙት የንግድ ተቋማት ውስጥ የሸቀጣ ሸቀጥ መደብር፣ ህንፃ መሳሪያዎች፣ የእህል መጋዘኖችና ወፍጮ ቤቶች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል። 

ሁሉም የንግድ  ተቋማት እንዲታሸጉ ተደርጉ እስከ አሁን  በአራት ነጋዴዎች ላይ ክስ የተመሰረተ ሲሆን በቀሪዎችም ላይ በህግ የማጣራት ስራ ተጀምሯል ።

በተመሳሳይ ሁኔታ የከንባታ ጠምባሮ ዞን ንግድና ገቢያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጸጋዬ መሀሩ  በዞኑ የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር የተዋቀረው ግብረ ኃይል ባደረገው ክትትል ህገ ወጥ ተግባር ሲፈጽሙ የተገኙ 170  ነጋዴዎች ተቋማቸው መታሸጉንና በህግ ለመጠየቅ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። 

የቁጥጥር ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ኃላፊው ህብረተሰቡም አጥፊዎችን በማጋለጥ መብቱን እንዲያስከብር  አሳስበዋል።

በከንባታ ጠምባሮ ዞን ዶዬገና ከተማ ነዋሪ አቶ ጌታሁን ለሎሮ በሰጡት አስተያየት አንዳንድ ነጋዴዎች የምርት እጥረት እንደተከሰተ በማስመሰል የዋጋ ጭማሪ በማድረጋቸው እሳቸውን ጨምሮ ድሀው ህብረተሰብ አስጨንቆ ሰንብቷል። 

የእለት ገቢዬ አነስተኛ በመሆኑ በዋጋው ንረት የተነሳ  ቤተሰባቸውን ለማስተዳደርም ሆነ የእለት ጉርስ ለመሸመት ስጋት ላይ ወድቄ ነበር  ብለዋል። 

የመንግስት አካላት ቁጥጥር ማድረግ ከጀመሩ ወዲህ ግን የዋጋ ንረቱ መቀነሱን ጠቁመው ክትትሉና የተወሰደው ርምጃ ቀጣይነት እንዲኖረው ጠይቀዋል። 

የወቅቱን ችግር ለማለፍ ቤት ውስጥ መሆን እንዳለባቸው በማመን አስፈላጊውን ግብዓት ለመግዛት ቢሞክሩም በሁሉም እቃዎች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ በመደረጉ መቸገራቸውን የተናገሩት ደግሞ በሆሳዕና ከተማ የሄጦ ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ እታለማሁ አየለ ናቸው። 

የበሽታው ወረርሽኝ እኛ ኢትዮጵያውያን እንድንረዳዳና  የሚያስተዛዝነን ሆኖ ሳለ በአንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች እየተደረገ ያለው ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ  ልንቃወመው ይገባልብለዋል።

በቅርቡ በተደረገው የዋጋ ቁጥጥር በሸቀጣ ሸቀጥና እህል ምርቶች ላይ ቅናሽ ማየታቸውን ገልጸው ቁጥጥሩ የዘወትር ስራ ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም