ጃክ ማ ሁለተኛ ዙር የኮሮናቫይረስ መከላከያ ቁሳቁሶችን ለአፍሪካ ሀገራት ላኩ - ኢዜአ አማርኛ
ጃክ ማ ሁለተኛ ዙር የኮሮናቫይረስ መከላከያ ቁሳቁሶችን ለአፍሪካ ሀገራት ላኩ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 28/2012 (ኢዜአ)የአሊባባ ፋውንዴሽን መስራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ ጃክ ማ ሁለተኛ ዙር የኮሮናቫይረስ መከላከያ ቁሳቁሶችን ለአፍሪካ ሀገራት ልከዋል።
በሁለተኛው ዙር ድጋፍ 500 የመተንፈሻ መሳሪያዎች (ቬንትሌተር)፣ 200 ሺህ የፊት መሸፈኛዎችና የህክምና ሙሉ ልብሶች፣ 2 ሺህ የሰውነት ሙቀት መለኪያ እና 500 ሺህ ጓንቶች ለአፍሪካ ሀገራት መላካቸውን የኢፌዲሪ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የጃክ ማ ፋውንዴሽን ከዚህ ቀደም የአፍሪካ ሃገራት የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያደርጉትን ጥረት ለማገዝ የሚውል የቁሳቁስ ድጋፍ መላኩ የሚታወስ ነው።
በመጀመሪያው ዙር የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19)ን ለመከላከል ለአፍሪካ 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን የምርመራ መሳሪያ፣ 6 ሚሊዮን የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ እና 60 ሺህ መከላከያ ልብሶች ድጋፍ አድርጓል።
በዚሁ መሰረት ከመጋቢት 13 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የድጋፍ ቁሳቆሶቹ ወደ አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን ድጋፉ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አማካኝነት ለአፍሪካ አገራት መሰራጨቱ የሚታወስ ነው።
ለአፍሪካ አገራት ድጋፉ እየተደረገ የሚገኘው የአሊባባ መስራች እና ባለቤት ጃክ ማ የአፍሪካ አገሮች የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ለሚያደርጉት ጥረት የሚውል ድጋፍ ለማድረግና ለማሰራጨት ባቋቋሙት ኢንሽዬቲቭ መሰረት ነው።
ጃክ ማ በውሃን የተቀሰቀሰውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመግታት የሚደረገውን ክትባት የማግኘት ርብርብ ለማገዝ የሚውል 14 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር በፋውንዴሽኑ በኩል መለገሱም አይዘነጋም።
የሁለተኛው ዙር የጃክ ማ የቁሳቁስ ድጋፍ እንደ መጀመሪያው ዙር ሁሉ በኢትዮጵያ በኩል የሚላክ መሆኑ ታውቋል።