በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ የምግብ ዘይትና ቤንዚን ተያዘ

50

ደብረ ብርሃን 27/07/2012 (ኢዜአ) በሰሜን ሽዋ ዞን ሽዋ ሮቢት ከተማ በህገ ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የተገኘ የምግብ ዘይትና ቤንዚን መያዙን የከተማዋ ፖሊስ ፅህፈት ቤት ገለፀ ። 

የከተማው ፖሊስ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር መርሃ ጽድቅ ታየ ለኢዜአ እንደገለፁት 800 ሊትር ዘይት በቁጥጥር ስር የዋለው በከተማው መግቢያ "ዙጢ" ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ትናንት ዘጠኝ ሰዓት ላይ ነው።

የምግብ ዘይቱ በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 አማ 22576 ሱዚኪ አነስተኛ የጭነት መኪና ተጭኖ በደሴ መስመር ወደ ሽዋ ሮቢት ከተማ ሊገባ ሲል ድንገት በተደረጋ ፍተሻ መያዙን ዋና ኢንስፔክተሩ ገልፀዋል።

ተሽከርካሪው ከዘይቱ በተጨማሪም ሰባት ሺህ ብር ግምት ያለው ጫት ይዞ ተገኝቷል ።

ያለ ህጋዊ ፈቃድ ሲጓጓዝ የተያዘው የምግብ ዘይቱ 56 ሺህ ብር ግምት ያለው ነው ተብሏል ።

የተሽከርካሪው ሹፌርና ረዳቱ በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳዩ እየተጠራ መሆኑንም ዋና ኢንስፔክተር መርሃ ፅድቅ ታየ ተናግረዋል ።

በተመሳሳይ መጋቢት 26 ቀን 2012 ዓም ማታ በአይሱዚ የጭነት ተሽከርካሪ 6 በርሜል ቤንዚን ከደብረ ብርሃን ወደ ሽዋ ሮቢት ከተማ ሊገባ ሲል በፀጥታ ኃይሎች ክትትል መያዙን የከተማዋ ፖሊስ አያይዞ ገልጿል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም