በቻይና ያሉ ተማሪዎችና ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ለኮሮና መከላከያ የሚውል 452 ሺህ በላይ ዩዋን ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
በቻይና ያሉ ተማሪዎችና ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ለኮሮና መከላከያ የሚውል 452 ሺህ በላይ ዩዋን ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 28/2012(ኢዜአ) በቻይና ያሉ ተማሪዎችና ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ለኮሮናቫይረስ መከላከያ የሚውል 452 ሺህ 589 ዩዋን ድጋፍ መደረጉን በቤጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ።
ከዚህም ውስጥ ከ100 ሺህ ዩዋን ያህሉ የህክምና መሳሪያዎች ተገዝተው እንደሚላኩበት ገልጿል።
ኤምባሲው እንዳስታወቀው የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭትን ለመግታት በኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ ኮሚቴ ተቋቁሞ በአገሪቱ ከሚገኙ ተማሪዎች፣ የኤምባሲ ማህበረሰብ ክፍሎች ከተለያዩ ከተሞች ነዋሪ ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ ተሰባስቧል።
በቻይና የሚገኙ የኢትዮጵያ ተማሪዎችና አቶ አስቻለው በላይ ከተባሉ የቤጅንግ ነዋሪ በድምሩ 101 ሺህ 189 ዩዋን ገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።
በሌላ በኩል በቤጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሰራተኞች 9 ሺህ 500 ዩዋን፣ ከተለያዩ የኢፌዴሪ ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች አባላት ማለትም ከጓንዦ 3 ሺህ ዩዋን፣ ከሻንሃይ 5 ሺህ 200 ዩዋን፣ ከክችንችን 211 ሺህ ዩዋን ሲሰበሰብ በጓንዦ ከተማ ዳያስፖራ አባላት ደግሞ 120 ሺህ ዩዋን ድጋፍ ተገኝቷል።
በዚህም በአጠቃላይ 452 ሺህ 589 ነጥብ 19 ዩዋን የገንዘብ ድጋፍ መሰብሰቡን አስታውቋል።
ከዚህም ውስጥ 351 ሺህ 400 ዩዋን በቀጥታ ቫይረሱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በኢትዮጵያ ለተቋቋመው ብሔራዊ ሀብት አሰባሳቢ ግብረ ኃይል መላኩን ገልጿል።
ቀሪው ከተማሪዎችና አቶ አስቻለው በላይ ከተባሉት የቤጂነግ ነዋሪ ኢትዮጵያዊ የተገኘው 101 ሺህ 189 ዩዋን ደግሞ የህክምና መሳሪያዎችን ገዝቶ ለመላክ ምርቶችን በማፈላለግ ላይ መሆኑን ኤምሳቢው አስታውቋል።
ከዚህም በተጨማሪ በኤምባሲው ውስጥ የሚገኙ ሁለት ኢምግሬሽንና የወሳኝ ኩነቶች ምዝግባ ኤጀንሲ ሰራተኞችና አንድ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባልደረባ በድምሩ ከ23 ሺህ ብር በላይ የሚሆን ከደመወዛቸው ተቆርጦ ለድጋፍ እንዲውል መወሰናቸውንም ኤምባሲው ገልጿል።