አባ ፍራንሲስ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ሰላማዊ ግንኙነት ለመፍጠር የተጀመረውን ጥረት አደነቁ

51
አዲስ አበባ 24/10/2010 የቫቲካኑ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን መሪ አባ ፍራንሲስ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ሰላማዊ ግንኙነት ለመፍጠር በሀገራቱ መሪዎች  የተጀመረውን ጥረት አደነቁ። አባ ፍራንሲስ ዛሬ በቫቲካን ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰበው ምእመን ባስተላለፉት መልዕክት “በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በርካታ ግጭት በሚስተዋሉበት በአሁኑ ወቅት ታሪካዊ ሊባል የሚችለውን ይህንን የመሰለ የሰላም ተነሳሽነት ማንሳት ግዴታችን ይሆናል” በማለት መናገራቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል። የኢትዮጵያና ኤርትራ መንግስታት ከሁለት አስርተ ዓመታት በኋላ በመካከላቸው ሰላም ለመፍጠር ተቀራርበው ለመነጋገር መወሰናቸው "ከሁለቱ አገራት ህዝቦች ባሻገር  በመላው አፍሪካ የተስፋ ብርሃን የሚፈነጥቅ ተግባር" መሆኑንም ገልፀዋል። የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ባለፈው ሳምንት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች በቅርቡ ተገናኝተው በመካከላቸው ሊኖር በሚገባው ሰላማዊ ግንኙነት ዙሪያ ይመክራሉ ብለዋል። የኤርትራ መንግስት ከፍተኛ የልኡካን ቡድንም ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጉ ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም