ቀጥታ፡

የጋምቤላ መምህራን ትምህርትና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ 1 ሺህ 86 ተማሪዎች አስመረቀ

ጋምቤላ ሰኔ 24/2010 የጋምቤላ መምህራን ትምህርትና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በተለያዩ የሙያ መስኮች በዲፕሎማ ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 86 ተማሪዎች አስመረቀ፡፡ ኮሌጁ በክልሉ በመካከለኛ ደረጃ የሚታየውን ብቃት ያለው የሰው ኃይል እጥረት ችግር ለመፍታት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሰናይ አኩዎር አሳስበዋል፡፡ የኮሌጁ ዲን አቶ ጓነር ማጆክ በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት ኮሌጁ ዛሬ በዲፕሎማ ያስመረቃቸው ተማሪዎች በትምህርትና በጤናው ዘርፍ በመደበኛው የትምህርት መርሃ ግብር ትምህርታቸውን ለሦስት ዓመታት የተከታተሉ ናቸው፡፡ ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል 511ቱ ሴቶች መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ ጓነር ገለጻ፣ በጤናው ዘርፍ የተመረቁ ተማሪዎች ከሰለጠኑባቸው የሙያ መስኮች መካከል ክሊኒካል ነርሲንግ፣ ላቦራቶሪ ቴክኒሻንና ጤና ኤክስቴሽን ይገኙበታል፡፡ ኮሌጁ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በትምህርትና በጤና ዘርፍ በመካከለኛ ደረጃ በክልሉ የሚታየውን የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ለመፍታት ያለሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በቀጣይም ያሉበትን የቤተ-ሙከራ፣ የማጣቀሻ መጻህፍት ችግሮችንና የመምህራንን አቅም በማጎልበት በዘርፉ ብቃት ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም ነው አቶ ጓነር የገለጹት። የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሰናይ አኩዎር በበኩላቸው በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ጥራቱን የጠበቀ የትምህርትና የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ኮሌጁ ብቃት ያለው ባለሙያ ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል፡፡ በእስካሁኑ ሂደት ኮሌጁ በክልሉ በትምህርትና በጤናው ዘርፍ በመካከለኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል በማሟላት በኩል የተሻለ ሥራ ቢያከናውንም በባለሙያዎች በኩል የሚታዩ ሙያዊ ክፍተቶችን በመሙላት በኩል በቀጣይ የተሻለ ስራ ሊሰራ እንደሚገባም አስግንዝበዋል፡፡ የክልሉ መንግስት በትምህርትና በጤናው ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በመደገፍ በኩል የዕለቱ ተመራቂዎች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ ለኢዜአ አስተያየት የሰጡት ተመራቂዎች በበኩላቸው በሰለጠኑበት የሙያ መስክ ሕብረተሰቡን ለማገልግለ ዝግጁ መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ከተመራቂዎች መካከል አያት አበባውና ፕላት ሎድ በሰጡት አስተያየት በሰለጠኑበት የሙያ መስክ ራሳቸውንና ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡ በተለይም በትምህርት ዘርፍ የሚታየውን የጥራት ችግር ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ የበኩላቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ነው ያስታወቁት፡፡                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም