የኮሮናቫይረስን በመፍራት ሳይሆን እርስ በርስ በመረዳዳት መከላከል ይቻላል - አቶ ኦባንግ ሜቶ

አዲስ አበባ መጋቢት 26/2012(ኢዜአ) የኮሮናቫይረስን በመፍራት ሳይሆን እርስ በርሳችን በመረዳዳት ማጥፋት እንችላለን ሲሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኦባንግ ሜቶ ገለፁ።

ከበሽታው ለመጠበቅ የሚተላለፉ መልዕክቶችን ችላ ለሚሉ ሰዎችም ያለማቋረጥ ደጋግሞ ትምህርት መስጠት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ ሜቶ ዜጋ ትልቅ ሀብት መሆኑን ገልጸዋል።

"ሁሉም ሰው በሚችለው አቅሙ መረዳዳት ከቻለ ወረርሽኙ የሚያስከትለውን ጉዳት መቀነስ እንችላለን" ብለዋል።

ዜጎች በወረርሽኙ ምክንያት ለጉዳት እንዳይጋለጡ ባለሃብቶች እያደረጉ ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።

አቶ ኦባንግ እንዳሉት፤ የበሽታውን መከላከያ መንገድ ሰምተው በትክክል የሚተገብሩ እንዳሉ ሁሉ የማይተገብሩም አሉ።

ሁሉም ሰው ስለበሽታው አደገኛነት ተገንዝቦ የራሱን ተገቢ ጥንቃቄ እንዲያደረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቱን በተደራጀ ሁኔታ ሳያቋርጡ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል ።

የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ በማኅበራዊ ትስስር ሚዲያ የተሳሳቱ መልዕክቶች የሚያስተላልፉ ሰዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኦባንግ አሳስበዋል።

ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨት ህዝቡ ላይ ሽብር በሚፈጥሩ አካላት ላይ መንግስት ጠንካራ ርምጃ መውሰድ መጀመሩ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም