ባንኩ ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት እደግፋለሁ አለ - ኢዜአ አማርኛ
ባንኩ ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት እደግፋለሁ አለ
መጋቢት 26/2012 (ኢዜአ) የምስራቃዊና ደቡባዊ አፍሪካ የንግድ እና ልማት ባንክ ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ጉዳትን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፍ አስታወቀ።
በኬንያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር መለስ ዓለም መቀመጫውን ናይሮቢ ካደረገው አህጉራዊ የንግድና ልማት ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጋር ውይይት አድርገዋል።
አምባሳደር መለስ ከዋና ስራ አስፈጻሚው አድማሱ ይልማ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት ባንኩ ኢትዮጵያ ኮሮናን መከላከል እንድትችል የህክምና ቁሳቁስ መግዛት የሚያስችል የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል።
ስራ አስፈጻሚው እንዳሉት ባንኩ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ የንግድና የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅሰው ለመንግሥት እና የግል ባንኮች ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት አንዳለውም ተናግረዋል።
አምባሳደር መለስ ዓለም ተቋሙ ለኢትዮጵያ ላሳየው አጋርነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በሌላ በኩል በናይሮቢ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆናቸውን አምባሳደሩ አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያዊያኑ ''ተደጋግፈን ይህንን የችግር ጊዜ እንለፍ'' በሚል መሪ ሀሳብ በአገር ቤት የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ በኤምባሲው በኩል ጥሪ ቀርቦላቸው ነው ድጋፍ በማድረግ ላይ የሚገኙት።
በኬንያ የኢትዮጵያ የኤምባሲ ዲኘሎማቶች ኮሮናን የመከላከል ዘመቻን ለመደገፍ የአንድ ወር ደመወዛቸውን ማበርከታቸውንም አምባሳደር መለስ ለኢዜአ አስታውቀዋል።