ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል የትምህርት ጥራት ችግርን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑ ተጠቆመ

አዳማ ሰኔ 24/2010 በትምህርት ዘርፍ ማነቆ የሆነውን የጥራት ችግር ከመሰረቱ ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ አስታወቀ። በክልሉ የዜጎችን አዕምሮ ለማልማት ልዩ ትኩረት መሰጠቱም ተመልክቷል። ለትምህርት ጥራት መጠበቅ እንቅፋት በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ኮንፈረንስ ከትናንት ጀምሮ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው። የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቶላ በሪሶ እንዳሉት የክልሉ መንግስት በትምህርት ዘርፍ ማነቆ የሆነውን የጥራት ችግር ከመሰረቱ ለመፍታት በትኩረት እየሰራ ነው። በተለይ በመምህራን አቅም ግንባታ፣ በግብዓት አቅርቦት፣ በሳይንሳዊ የትምህርት አመራር አተገባበርና የትምህርት ጥራት ክበባትን በማጠናከር ላይ ትኩረት አድርጎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስረድተዋል። "ከክልሉ ጠቅላላ ህዝብ አንድ ሶስተኛ የሚሆነው በትምህርት ገበታ ላይ ይገኛል" ያሉት ዶክተር ቶላ፣ ይህ ኃይል በቀጣይነት የሀገሪቷን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ቀጣይነት የሚወስን መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም የትምህርት ዘርፉን ጥራትና ብቃትን ማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ መምራት እንደሚገባ አስገንዘበዋል። ኮንፈረንሱም በ2010 ዓ.ም በዘርፉ የተመዘገቡ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመገምገም በቀጣዩ የበጀት ዓመት የትምህርት ጥራትን ለማጎልበት ያለመ መሆኑን ነው የገለጹት። የፖለቲካ አመራሮች ቁርጠኝነትና ዕገዛ፣ የህብረተሰቡ ተሳትፎና የሙሁራን ድርሻን በግልጽ ለይቶ ለማስቀመጥና ለዕቅዱ ተግባራዊነት በጋራ ለመረባረብ አቅጣጫ የሚቀመጥበት መሆኑንም ተናግረዋል። ዶክተር ቶላ እንዳሉት በክልሉ ከሚገኙት ከ15ሺህ 900 በላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ አብዛኛው ከደረጃ በታች ናቸው። በመድረኩ ላይ የቀረበው ጥናታዊ ጽሁፍም በክልሉ ከሚገኙት ትምህርት ቤቶች 95 በመቶ የሚሆኑት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርተ ቤቶች እንዲሁም 30 በመቶ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቤተ ሙከራ እንደሌላቸው አመልክቷል። በተመሳሳይ ከ60 እስከ 75 በመቶ የሚሆኑት የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በቂ የትምህርት መርጃ መሳሪያ፣ ንፁ የመጠጥ ውሃ፣ መብራት፣ ሽንትቤትና ሌሎች ተያያዥ ግብዓት ያልተሟላላቸው መሆናቸውን ነው የገለጸው። "ይህን ችግር ለመፍታት የተቀናጀ የህብረተሰቡና የመንግስት ርብርብ ያስፈልጋል" ያሉት ኃላፊው ኮፍረንሱም ችግሩን በጋራ የመፍታት አላማ እንዳለው አመልክተዋል። እንደዶክተር ቶላ ገለጻ፣ የተቋማቱን መሰረተ ልማቶች በተለይም የመብራት ችግር ለማፍታት በሁሉም ትምህርት ቤቶች  አይሲቲን ማንቀሳቀስ የሚችል ሶላር ለመትከል ትምህርት ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ ይገኛል ። በ2011 የበጀት ዓመት ከ25 ሚሊዮን በላይ የመማሪያ መጻህትንና የትምህርት መርጃ መሳሪያዎች ለማቅረብም ዕቅድ ተይዟል። የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ አዳነች ሀቤቤ በበኩላቸው የክልሉ መንግስት ከሁሉም በፊት የዜጎችን አዕምሮ ማልማት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል። ዜጎችን የትምህርት እድል ተጠቃሚ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ማፍራት የሚቻልበት ሥራዓተ ትምህርት መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል። "በአሁኑ ወቅት ጥያቄ ውስጥ ያለው የትምህርት ጥራት ዋነኛ ችግር በፖለቲካ አመራሩ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆንና በዕውቀት ያለመምራት ነው" ብለዋል። በአዳማ ከተማ ለሁለት ቀናት በሚቆየው ኮንፈረንስ ላይ ከ1ሺህ 500 በላይ የሚሆኑ ከክልሉ ሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች የተወጣጡ የትምህርት፣ የፋይናንስ፣ የአስተዳደር፣ የመምህራን ማህበርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ መሆናቸው ታውቋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም