በአሶሳ ከተማ በውሃ እጥረት መቸገራቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
በአሶሳ ከተማ በውሃ እጥረት መቸገራቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ
አሶሳ (ኢዜአ)መጋቢት 25/ 2012 ፡- ንጽህናቸውን በመጠበቅ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ጥረት እያደረጉ ቢሆንም በውሃ እጥረት መቸገራቸውን በአሶሳ ከተማ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ከነዋሪዎቹ መካከል ወይዘሮ ገነት ለገሰ እንሉት እጃቸውን በመታጠብ እና ከአካላዊ ንክኪ በመራቅ ራሳቸውን ከበሽታው ለመከላከል ጥረት እያደረጉ ነው፡፡
ሆኖም በከተማው ውሃ ለሳምንታት እንደሚቋረጥ እና ስርጭቱም ቢሆን ፍትሃዊ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
ችግሩን እንዲፈታላቸው በተደጋሚ ለአስተዳደሩ አሳውቀው መፍትሔ ማጣታቸውንም አመልክተዋል፡፡
በዚህም ምክንያት ንጽህናቸውን በመጠበቅ ኮሮናን ለመከላከል የሚያደጉትን ጥረት እንቅፋት እንደሆነባቸው ወይዘሮ ገነት ተናግረዋል።
በከተማው ከሚኖሩ አስር የበጎ ፈቃደኛ ማህበራት መካከል የውማ በጎ አድራት ወጣቶች ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ሰይድ ዓሊ በበኩሉ የማህበሩ አባላት ሳምንቱን ሙሉ በከተማው በበጎ ፈቃድ የህብረተሰቡ እጅ በማስታጠብ ላይ መሰማራታቸውን ገልጿል።
"በውሃ እጥረት ምክንያት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራው በሳምንት ሁለት የገበያ ቀናት ብቻ ለማከናወን ተገደናል "ብለዋል፡፡
በእነዚህ ቀናትም ቢሆን ከኪሳቸው አዋጥተው ባሰባሰቡት ገንዘብ አንድ ጀሪካን ውሃ እስከ ሰባት ብር እንደሚገዙ የገለጸው ወጣት ሰይድ አስተዳደሩ ውሃ ለማቅረብ ቃል ቢገባም ተግባራዊ ባለማድረጉ መቸገራቸውን ተናግረዋል።
"ህብረተሰቡን በሚገባ ማገልገል እየፈለግን በውሃ እጥረት ተገድበዋል " ያለው ወጣት ሰይድ አባላት በቀጣይ ውሃ ቢቀርብላቸው ህዝባቸውን በነጻ ማገልገላቸውን ለመቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
ስለጉዳዩ የተጠየቁት የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኡመር መሃመድ በሰጡት ምላሽ በከተማው የህብረተሰቡ ቁጥር በፍጥነት መጨመር የውሃ እጥረት እንዳስከተለ ገልጸዋል፡፡
አስተዳደሩ ለችግሩ የአጭር እና የረጅም ጊዜ መፍትሔ አስቀምጦ እየሠራ ነው ብለዋል።
ውሃ በቦቲ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተው ተጨማሪ ሁለት ጥልቅ የመጠጥ ውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮ በመጠናቀቁ በቅርቡ አገልግሎት ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የከተማው በጎ ፈቃደኞችን ተግባር በውሃ አቅርቦት ለመደገፍ የተደረገ ጥረት መኖሩን ጠቁመው ሆኖም ለነዋሪው ቅድሚያ በመሰጠቱ በሚያስፈልጋቸው ልክ እንዳልተዳረሰ አስረድተዋል፡፡
"ውሃን በፍትሐዊነት በማቅረብ ረገድ ችግሮች መኖራቸውን አስተዳደሩ ይረዳል "ያሉት ከንቲባው ችግሩን ለመፍታት የከተማው ውሃ አቅርቦት በኮማድ ፖስት እንዲመራ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
በአራት ቀናት አንዴ ለማዳረስ የወጣውን የውሃ ፕሮግራም የሚያዛቡ ሠራተኞች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመው አስተዳደሩ እርምጃ ለመውሰድ ጉዳዩን እያጣራ ነው ብለዋል፡፡
ነዋሪው ተጨባጭ መረጃ በመስጠት እንዲተባበር ከንቲባው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በክልሉ የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል በከተማው የሚታየውን የውሃ እጥረት ዋነኛ አጃንዳው እንዳደረገ የገለጹት ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን ናቸው።
ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት የተጀመሩ ስራዎች በጥቂት ቀናት እንዲጠናቀቁ ግብረኃይሉ የቅርብ ክትትል እያደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
በአሶሳ ከተማ 100 ሺህ የሚጠጋ ህዝብ እንደሚኖር ከአስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡