የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎች ላይ እርምጃ አንዲወሰድ የአፍሪካ ህብረት አሳሰበ

አዲስ አበባ ሰኔ 24/2010 በደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ግጭት ቁልፍ ተዋናዮች ላይ ጠንካራ እርምጃ አንዲወሰድ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሐመት ጥሪ አቀረቡ። ሊቀመንበሩ በሞሪታኒያ ርእሰ መዲና ናውክቾች ዛሬ በተጀመረው 31ኛ የህብረቱ አባል ሀገራት የመሪዎች ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት በደቡብ ሱዳን በአሁኑ ወቅት ያለው ሁኔታ በእጅጉ አሳሳቢ ነው። በሀገሪቱ ያለው የሰብዓዊና የፀጥታ ችግር እየተባባሰ መጥቶ በአሁኑ ወቅት አስቸጋሪ ደረጃ ላይ መድረሱን የገለፁት ኮሚሽነሩ ባለፈው ሳምንት በሁለቱ የሀገሪቱ ተፋላሚ ወገኖች መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ከወዲሁ አደጋ ላይ መውደቁንም ጠቁመዋል። "በግጭቱ ቁልፍ ተዋናይ የሆኑት አካላት በየጊዜው የሚገቡትን ቃልኪዳን ባለማክበር በድርጊታቸው ተሰልችተናል" ሲሉም ነው ኮሚሽነሩ የተናገሩት። የዚህ ዓይነቱ ተግባር ከአሁን በኋላ በዝምታ መታለፍ የሌለበት ነው ያሉት የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ፤“ኃላፊነታችንን እንዲቀበሉ ለማድረግ የሚያስችል እርምጃ የምንወስድበት ወሳኝ ወቅት ላይ ነን ” ሲልም አሳስበዋል። በግጭቱ ዋነኛ የሆኑት ወገኖች የሚገቧቸውን ቃል ኪዳኖች ያከብሩ ዘንድ ግልፅ መልዕክት ሊተላለፍላቸው ይገባል በማለትም የሚደረግ ማእቀብ ሊኖር እንደሚችል ሊቀመንበር ማስጠንቀቃቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና ተቀናቃኛቸው ዶክተር ሪክ ማቻር ባለፈው ሳምንት በሱዳን ካርቱም በተካሄደው የሰላም ድርድር ላይ የተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማምተው የነበረ ቢሆንም ከሰዓታት በኋላ ስምምነቱ መጣሱ ተዘግቧል። ለዚህም ሁለቱ ወገኖች እርስ በእርሳቸው በመወነጃጀል ላይ መሆናቸውም ተመልክቷል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሁለቱ ወገኖች የፖለቲካ ስምምነት ላይ እንዲደረሱ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር አስከተጠናቀቀው ሰኔ ወር ድረስ ቀን ቆርጦላቸዋል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ይህን ማድረግ ከተሳናቸው ግን ማእቀብ እደሚከተላቸውም ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸዋል። ከዚህ ቀደም በሁለቱ ጎራዎች መካከል የተደረሱት የተኩስ አቁም ሰምምነቶች በተደጋጋሚ ሲጣሱ ቆይተዋል። በደቡብ ሱዳን ላለፉት አምስት ዓመታት በቆየው የእርስ በእርስ ግጭት ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ ለስደት ተዳርጓል። ከዚህም ሌላ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን የሚሆን ህዝብ ከቀዬው ተፈናቅሏል፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል። በአሁኑ ወቅት ሰባት ሚሊዮን የሚሆን የሀገሪቱ ዜጋ ደግሞ የሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልገዋል። ጠቅላላ የህዝብ ብዛቷ 12 ሚሊዮን እንደሚሆን የሚገመተው ደቡብ ሱዳን አዲስ ሀገር ሆና በዓለም ካርታ ውስጥ ከገባች ገና የሰባት ዓመት አድሜ ያስቆጠረች ናት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም