ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በወንበር ልክ ብቻ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ጀመረ

አዲስ አበባ ፤መጋቢት 25/2012 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር የትራንስፖርት አገልግሎቱን ከዛሬ ጀምሮ በወንበር ልክ ብቻ ማድረጉን አስታወቀ።

ከባቡሩ ጎን ለጎን የጎልዴን ባስ ትራንስፖርት ተመሳሳይ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑም ታውቋል።


የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት ከዛሬ ጀምሮ ተሳፋሪዎችን በወንበር ልክ ብቻ በመጫን አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልጿል።

የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ስንታየሁ ወልደሚካኤል እንደገለጹት ከዚህ ቀደም ባቡሩ በቀን በአማካይ 110 ሺህ ሰዎችን ያስተናግድ ነበር።

የኮሮናቫይረስ በኢትዮጵያ ከተከሰተ በኋላ ደግሞ እለታዊ የማስተናገድ አቅሙን ወደ 45 ሺህ ሰዎች ዝቅ አድርጎ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ሰርቷል።

ሆኖም የቫይረሱ ስርጭት እንዳይኖርና በተገቢው ርቀት ለማስተናገድ ሲባል የትራንስፖርት አገልግሎቱን ከዛሬ ጀምሮ በወንበር ልክ ብቻ አድርጓል።

ከባቡሩ ጎን ለጎን 10 የጎልደን ባሶች ከአያት እስከ ጦር ሃይሎች እንዲሁም ከጊዮርጊስ እስከ ቃሊቲ የባቡር መስመሩን ተከትለው የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን ዶክተር ስንታየሁ ገልጸዋል።

አውቶቡሶቹ ይህንን አገልግሎት እንዲሰጡ ድጋፍ ያደረጉት በላይነህ ክንዴ የተባሉት ባለሃብት መሆናቸውም ታውቋል።

በቀጣይ የተሳፋሪዎች ቁጥር እየታየ የባሶቹ ቁጥር ከፍ እንዲል የሚደረግ መሆኑም ተገልጿል።

የኮሮናቫይረስ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ሆኖ የበርካታ አገራት ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ከሆነ ወራቶች እየተቆጠሩ ነው።

በዓለም ላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር  ከ1 ሚሊዮን ሲሻገር የሟቾች ቁጥርም ከ50 ሺህ በልጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም