ቀጥታ፡

ሁለት ተቋማት ለኮሮና ቫይረስ መከላከል የ15 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ

መቀሌ/ኢዜአ/መጋቢት 25/2012ዓም በትግራይ ክልል የኮኖና ቫይረስ ለመከላከል የተቋቋመው ጊዜያዊ ኮማንድ ፖስት ከሁለት ተቋማት የ15 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አገኘ።
ደደቢት ማይክሮ ፋይናንስና ተከዜ የጥልቅ ውሀ ጉድጓዶች ቁፋሮ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር  የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመከላከል በክልል ደረጃ ለተቋቋመው ኮማንድ ፖስት የ15 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ዛሬ አስረክበዋል።

 ኮማንድ ፖስቱ ቫይረሱን ለመከላከል የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግለት ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ ደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ  የ10 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን የድርጅቱ ዋና ስራ አስክያጅ አቶ ሙሉጌታ ብርሀነ ገልጸዋል።

ተከዜ የጥልቅ ውሀ ጉድጓዶች ቁፋሮ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በበኩሉ የ5 ሚልዮን ብር ድጋፍ አድርጓል።

በኮማንድ ፖስቱ የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢና የክልሉ ፋይናንስና እቅድ ቢሮ ሀላፊ አቶ ዳንኤል አሰፋ እንደገለጹት ሁለቱም ተቋማት ያደረጉት ድጋፍ ቫይረሱን የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ፈጣን ግብረ መልስ ለመስጠት የሚረዳ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ከፍተኛ የድህነት መጠን በመኖሩ ለበሽታዎች ተጋላጭ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው ያሉት አቶ ዳንኤል ይህንኑ ለመከላከል ክልሉ ለቫይረሱ መዛመት ምክንያት ይሆናሉ ያላቸውን ጉዳዮች ክልከላ ማስቀመጡን ገልፀዋል።

ክልሉ ያስቀመጣቸው ክልከላዎች የህዝቡን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል የተደረገ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ    ሁሉም እንዲሳተፍ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም