አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ ህብረተሰቡ ከኮሮናን እንዲጠብቅ የጥንቃቄ መልእክት አስተላለፍ - ኢዜአ አማርኛ
አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ ህብረተሰቡ ከኮሮናን እንዲጠብቅ የጥንቃቄ መልእክት አስተላለፍ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2012 (ኢዜአ) አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር ህብረተሰቡ ከኮሮናቫይረስ ራሱን እንዲጠብቅ የጥንቃቄ መልእክት አስተላለፍ።
አርቲስት ሰራዊት በመዲናዋ ሜክሲኮ፣ ብሔራዊ ቲያትር አካባቢ በመዘዋወር ሁሉም ሰው ስለቫይሩሱ ያለውን ግንዛቤ በየጊዜው በማሳደግ ራሱን፣ ቤተሰቡንና አገሩን ካንዣበበው አደጋ መጠበቅ እንዳለበት ተናግሯል።
“በጥንቃቄ ኖረን ይህን ቀን እንደምናልፈው አምናለው" ያለው አርቲስቱ በአስከፊው የኮሮናቫይረስ ዓለም ግራ መጋባቱንና ታላላቅ የተባሉ የበለጸጉ አገሮች ጭምር ፈተና ውስጥ መውደቃቸውን አመልክቷል።
"ኢትዮጵያዊያን ይህንን አስቸጋሪ ወቅት ለማለፍ ብርቱ ጥንቃቄና ግንዛቤ ያስፈልገናል" ሲልም ተናግሯል።
"ወጣቶች በሰላም ኖረው ነገ ለወግ ማእረግ እንዲበቁ፤ ጥንዶችም ወልደው ለመሳምና ልጆችን ለማሳደግ እንዲችሉ ዛሬን መጠንቅቅ የግድ ነው" ያለው አርቲስት ሠራዊት፣ ሁሉም ሰው ሳይዘናጋ ራሱንና ሌላውን ከቫይረሱ እንዲከላከል መክሯል።
“ህብረተሰቡ በተወሰነ መልኩ የሚተላለፉ የጥንቃቄ መልዕክቶችን እየተገበረ ቢሆንም አሁንም ቸልተኝነት ይስተዋላል፤ ይህን ቸልተኝነት ለማስወገድ ዛላቂ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠት ያስፈልጋል" ብሏል።
በተለይ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ተከታታይነት ያለው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሊስጡ እንደሚገባም አመልክቷል።
በማንኛውም አጋጣሚና ቦታዎች ላይ ሁሉም ሰው አካላዊ ርቀቱን ከመጠበቅ ጎን ለጎን የግል ንጽህናውን በአግባቡ በመጠበቅ የኮረናቫይረስን በጋራ ማስቆም እንደሚገባም ገልጿል።
በኢትዮጵያ እስካሁን 29 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን እስካሁን ሶስቱ ማገገማቸውም ታውቋል።