የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅ በአገራዊ አንድነት ስሜት ርብርብ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅ በአገራዊ አንድነት ስሜት ርብርብ እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 24/2012 (ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅ በአገራዊ አንድነት ስሜት ርብርብ እየተደረገ መሆኑ ተገለፀ።
ለግድቡ ግንባታ እስካሁን ከህዝቡ 13 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በድጋፍ መልክ መሰብሰቡም ታውቋል።
የሕዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበት 9ኛ ዓመት በአዲስ አበባ በፓናል ውይይት ተከብሯል።
የፓናል ውይይቱ የተደረገው ስለግድቡ ያሉ ወቅታዊና አዳዲስ መረጃዎችን ለህዝቡ ለማድረስ እንዲሁም በመንግስት በኩል ያለውን ቁርጠኝነት ለማሳየት ታስቦ መሆኑ ታውቋል።
በፓናል ውይይቱ ላይ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ እና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ ተሳትፈዋል።
በውይይቱ መክፈቻ ላይ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ግደቡ ያለበትን ደረጃ በሚመለከት ማብራሪያ ሰተዋል።
የግድቡ የግንባታ ሂደት አፈፃፀም የሲቪል፣ የኤሌክትሮ መካኒካል እና የብረታ ብረት ስራዎችን ጨምሮ የኮንክሪት፣ የብረታ ብረትና የጎርፍ ማስተንፈሻ ሥራዎች በጥሩ አፈፃፀም ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
የግድቡ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎቹ አፈፃፀም ከ42.3 በመቶ በላይ ሲሆን የሲቪል ስትራክቸር የግንባታ ሒደትም ከ20 በመቶ በላይ ተከውኗል።
አጠቃላይ የኘሮጀክቱ አሁናዊ የአፈፃፀም ሂደትም ከ72 ነጥብ 4 በመቶ በላይ መድረሱን ኢንጂነር ክፍሌ ገልጸዋል።
የግንባታ ሰራተኞች ከዋና ኃላፊዎች እስከ ታች በከፍተኛ የሥራ ሞራል በህዝብና መንግስት የተሰጣቸውን አደራ ለመወጣት እየሰሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
"በኮሮናቫይረስ ምክንያት የግድቡ የግንባታ ሂደት እንዳይደናቀፍ ለሠራተኞች አስፈላጊውን የመከላከያ ግብዓት ቀርቦላቸው እየሰሩ ይገኛሉ" ብለዋል።
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፣ በግድቡ ላይ ኢትዮጵያ ያላትን አቋም እና ከግብጽ ጋር ሲደረጉ የቆዩ የድርድር ሂደቶችን አስመልክቶ ገለፃ አድርገዋል።
በአሁኑ ወቅት የግድቡ ግንባታ ከምንጊዜውም በላይ በአገራዊ አንድነት ስሜት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገለፀው ኢትዮጵያ ከተፋሰሱ አገሮች ጋር ትብብሯን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው ሀብት ላይ የሚነሱ እኔ ብቻ ልጠቀም የሚሉ ጥያቄዎችን በእውቀት መመከት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋለ።
ለግድቡ ግንባታ እስካሁን ከህዝቡ ወደ 13 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በድጋፍ መልክ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ደግሞ የጉልበት ድጋፍ ተደርጓል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ፣ ከለውጡ በኋላ በተሰጠ ጠንካራ አመራር ለዓመታት የዘገየውን የግንባታ ሂደት በፍጥነት በማካሄድ ከወራት በኋላ የግድቡ የውሃ ሙሌት እንደሚጀምር ገልፀዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ በበኩላቸው በግድቡ የህብረተሰብ ተሳትፎ ሂደትን በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል።
ህዝቡ እስካሁን በገንዘብ፣ በእውቀት እና በጉልበቱ ሲያደርገው የነበረውን ድጋፍ መቀጠሉን ጠቁመው፣ በአሁኑ ወቅት የግድቡን ግንባታ ከጫፍ ለማድረስ የሚያስችል ቁጭት በህብረተሰቡ ዘንድ መፈጠሩን ተናግረዋል።
በታህሳስ 2013 ዓ.ም የግድቡ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት የሚጀምሩ ሲሆን ግድቡ ሲጠናቀቅም 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የመያዝ አቅም ይኖረዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠው መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም መሆኑ ይታወቃል።