ቀጥታ፡

የገቢዎች ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ ለኮሮና መከላከያ የ15 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ መጋቢት 24/2012 (ኢዜአ) የገቢዎች ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የ15 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በእዚህ ወቅት እንዳሉት በድጋፍ የተሰጡት ሸቀጦች በተለያዩ ጊዜያት በህገ ወጥ መንገድ ሲገቡ የተያዙና ለምግብ ፍጆታነት የሚውሉ መሰረታዊ ሸቀጦች ናቸው።

በድጋፉ እንደ ስንዴ፣ ዘይት፣ ሩዝና መሰል የምግብ ፍጆታቸዎች ድጋፍ መደረጋቸውን ገልጸዋል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሙሉ በሙሉ እስኪጠፋ ድረስ ተቋሙ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስን ለማጥፋት የጋራ ርብርብና ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

በዛሬው እለትም የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የጉሙሩክ ኮሚሽንና የብሔራዊ ሎተሪ ሠራተኞችና አመራሩ በጋራ በመሆን የ2 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርገዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ ሚኒስቴሩ ከጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ግምታቸው ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ የምግብ ሸቀጦችን ድጋፍ አድርጓል።

በዓይነት ከተደረገው ድጋፍ መካከል ከ4 ሚሊዮን 768 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው የምግብ ፍጆታዎች በፌዴራል ደረጃ ለተዋቀረው የገቢ አሰባሳቢ ግብረ ኃይል አስረክበዋል።

ከ7 ሚሊዮን 930 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ የምግብ ፍጆታዎችም በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ስር ለተዋቀረው የገቢ አሰባሳቢ ግብረ ኃይል ድጋፍ ማደረጉን አስረድተዋል።

ተቋማቱ በጋራ ለሚደግፏቸው 186 ህጻናት በየወሩ ከሚደረገው እገዛ በተጨማሪ የኮሮናቫይረስ ያስከተለውን ኢኮኖሚያዊ ቀውስ መቋቋም እንዲችሉ ከ300 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ ማድርጋቸውን ሚንስትሩ ገልጸዋል።

በመሆኑም የገቢዎች ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል በጥቅሉ የ15 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም