ቀጥታ፡

የልብ ኃኪሞች ህብረተሰቡ ከኮሮና ቫይረስ እንዲጠነቀቅ አሳሰቡ

አዲስ አበባ መጋቢት 24/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ ማዕከል ሃኪሞች በአዲስ አበባ ጎዳናዎች በመዘዋወር ህብረተሰቡ የኮሮና ቫይረስን እንዲከላከል የጥንቃቄ መልእክት አስተላለፉ።

የኢትዮጵያ ልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ ማዕከል ጤና ባለሙያዎች መደረግ ስላለበት ቅድመ ጥንቃቄ ለአምስት ቀናት የሚቆይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠት ጀምረዋል።

የኮሮና ቫይረስ አሳሳቢነት ከአገር መሪዎች እስከ ጤና ሙያተኞች በማስጨነቅ በየአገራቱ ዜጎች ከወረርሽኙ ራሳቸውን እንዲከላከሉ ጥሪ መቅረብ ከጀመረ ውሎ አድሯል።

ኮሮና በኢትዮጵያ መግባቱ ከተረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮም መንግስት የተለያዩ የጥንቃቄ እርምጃዎችን እየወሰደ ቢሆንም በህዝቡ ዘንድ የሚደረገው ጥንቃቄ ግን የሚጠበቀውን ያህል እንዳልሆነ ተደጋግሞ ይነገራል።

ይህን ተከትሎ ሁሉም በየሙያ መስኩ የፀረ ኮሮና ቫይረስ ንቅናቄ እያደረገ ይገኛል።

ዶክተሮቹንና ነርሶችን ያካተተ የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ ማዕከል የጤና ባለሙያዎች ቡድንም ስለበሽታው አስከፊነት ግንዛቤ ለማስጨበጥ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ከስራ ቦታ ወደ ጎዳናዎች ወጥተዋል።

ቡድኑ በዛሬ ውሎው ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከሚገኘው ማዕከሉ መነሻውን በማድረግ በተክለሃይማኖት፣ አትክልት ተራ፣ አውቶቡስ ተራና መርካቶ የገበያ ማዕከላት በመዘዋወር የጥንቃቄ መልዕክት አስተላልፏል።

በመልእክታቸውም አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ የእጅ ንጽህናን መጠበቅ፣ ከእጅ ሰላምታ መቆጠብ፣ ሳይታጠቡ ፊትና አፍንጫን አለመነካካት፣ ከመሰባሰብ መቆጠብና ሌሎችንም መልእክቶች አድርሰዋል።

የቡድኑ አስተባባሪና በማዕከሉ የህጻናት ልብ ኃኪም ዶክተር ይልቃል ጫኔ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት "ህብረተሰቡ የወረርሽኙን አደገኛነት በቅጡ የተገነዘበው አይመስልም" ብለዋል።

ቫይረሱ በኢትዮጵያ አሁን ያለበት ደረጃ ከጤና ተቋማቱና ከባለሙያዎች አቅም በላይ ሊሆን እንደማይችል ገልጸው፤ ነገር ግን ህብረተሰበቡ አሁን ባለው የቅድመ ጥንቃቄ ጉድለት ከቀጠለ ጉዳቱ የከፋ የሆናል ብለዋል።

"ወራጅ ውሃን ሳይደርስ ከመጠንቀቅና ከደረሰ በኋላ የነብስ አድን ስራ ከመስራት" የተሻለውን አማራጭ ሁሉም ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባት እንደሚገባው ገልጸዋል።

ህብረተሰሰቡም ከመንግስትና ከጤና ሙያተኞች የሚሰጡትን የጥንቃቄ መልእክቶች ተግባራዊ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

በሌሎች አገራት ወረርሽኙ በተዛመተበት አኳኋን በኢትዮጵያም ቢከሰት አገሪቷ ባላት የጤና ተቋማት ብዛት፣ የጥራት ደረጃና የባለሙያዎች አቅም ልትቋቋመው እንደማትችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

"በመሆኑም ጥፋቱ ደርሶ ጉዳት ከመድረሱ በፊትም አስቀድሞ መጠንቀቅ ይገባል" ብለዋል።

ወረርሽኙን ለመከላከል ህብረተሰቡ ብቻ ሳይሆን የጤና ባለሙያዎችም መስራት ያሉባቸውን ተግባራት እንዲተገብሩ ጠቁመዋል።

ሃኪሞቹ ሞያዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው፤ ብዙ መሰራት ያለባቸው ስራዎች እንዳሉም ጠቅሰዋል።

በቀጣይ የመገናኛ ብዙሀንም ሆኑ በተለያየ የሙያ መስክ የሚገኙ ዜጎች ለህብረተሰቡብ የግንዛቤ ፈጠራ ተግባራትን ማጠናከር ይኖርባቸዋል ብለዋል።

የሃኪሞቹ የግንዛቤ ማስጨበጥ ቅስቀሳ ከዛሬ መጋቢት 24 እስከ 28 ቀን 2012 ዓ.ም ለተከታታይ አምስት ቀናት በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች ይቀጥላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም