ቀጥታ፡

ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የጋምቤላ ክልል ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል--- ኡሞድ ኡጁሉ

ጋምቤላ መጋቢት 24/2012 (ኢዜአ) ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እውን መሆን የክልሉ መንግስትና ህዝብ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ አጁሉ አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳደሩ የግድቡ ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ የተቀመጠበትን ዘጠነኛ ዓመት አስመልከተው ለኢዜአ እንደገለጹት የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የክልሉ ህዝብና መንግስት በስጦታና በቦንድ ግዥ ድጋፍ ሲያደረግ ቆይቷል።

በቀጣይም አሁን ላይ ፈተና እየሆነ ያለውን የኮሮና ቫይረስ በመከላከል የኢትዮጵያ ህዝቦች የአንድነት መገለጫ ለሆነው የግድቡ ግንባታ የክልሉ መንግስትና ህዝብ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

በቅርቡ በግድቡ ግንባታ ዙሪያ በግብጽ  የቀረበውን ሃሳብ በመደገፍ የአሜሪካ መንግስት ጫና ለመፍጠር ያደረገው ሙከራ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የማይጠበቅ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

በአሜሪካ መንግስት የታየውን አድሎዊ ድርጊትም የክልሉ መንግስትና ህዝብ አጥብቆ እንደሚቃወመው ገልጸዋል።የግድቡ ግንባታ ፍፃሜውን እስኪያገኝ የክልሉ ህዝብ በእኔነት ስሜት የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ርዕሰ መስተዳደሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የክልሉ የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪ ጽህፈት ቤት ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተንኳይ ጆክ  በበኩላቸው ካሁን በፊት ለግድቡ ግንባታ የክልሉ ህዝብና መንግስት በስጦታና በቦንድ ግዥ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማደረጋቸውን አመልክተዋል።

በተያዘው ዓመታም የህዝብ ንቅናቄ በመፈጠር ለግድቡ ግንባታ የሚያግዝ ተጨማሪ ድጋፍ ለማስበሰብ እቅድ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም