ቀጥታ፡

ምዕመናን የአምልኮ ስርዓታቸውን በያሉበት ቦታ ሆነው እንዲያከናውኑ ጥሪ አቀረበ

አዲስ አበባ፣መጋቢት 24/2012 (ኢዜአ) የኮሮናቫይረስ  ስርጭትን ለመከላከል ሲባል ምዕመናን የአምልኮ ስርዓታቸውን ባሉበት ሆነው እንዲያከናውኑ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጥሪ አቀረበ።

ጉባኤው ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንደገለጸው፤ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ከወዲሁ ጥንቃቄ መደረግ አለበት።

በኢትዮጵያ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል በተለያዩ እምነት ተቋማት በኩል የተወሰነው ውሳኔም ወቅታዊና ሃይማኖታዊ አስተምህሮን መነሻ በማድረግ መሆኑን ገልጿል።

ውሳኔው በዋናነት ያስፈለገው የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ሁሉም ሃላፊነቱን በአግባቡ ካልተወጣ ችግሩ ሊባባስ እንደሚችል መገንዘብ አስፈላጊ እንደሆነ አመልክቷል።

በመሆኑም ምዕመኑ በሐይማኖት አባቶችና በጤና ባለሙያዎች የተላለፈውን ውሳኔ ተግባራዊ እንዲያደርጉ ነው የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ያሳሰበው።

ምዕመናን ባሉበት ቦታ ሆነው እንደየእምነት ስርዓታቸው ጸሎት በማድረግና ንስሃ በመግባት ፈጣሪያቸውን በጸሎት መለመን ይገባቸዋል ሲል ጥሪውን አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም