ቀጥታ፡

ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ጥንቃቄ ማድረግ ከእምነት ጋር እንደማይጋጭ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣መጋቢት 24/2012 (ኢዜአ) ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ጥንቃቄ ማድረግ ከእምነት ጋር እንደማይጋጭ የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ገለጸ። ካውንስሉ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ያከናወነውን የስራ ሪፖርት ትናንት አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ወንገላዊት ቤተ ክርስቲያን ካውንስል የኢትዮጵያ የመካነ ኢየሱሰ አብያተ ክርስቲያናት ህብረት፣ የኢትዮጵያ ቃለ ህይወት ቤተ ክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ቪዥነር አብያተ ክርስቲያን ህብረት፣ የኢትዮጵያ ጰንጤ ቆስጣል አብያተ ክርስቲያናት ህብረት፣ የኢትዮጵያ ኢንዲፐንዴት አብያተ ክርስቲያናት ህብረትን ያካተተ ነው።

ካውንስሉ በፌዴራል እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለተቋቋመው የኮሮናቫይስ መከላከል ግብረ ሃይል ባቀረበው ሪፖርት ምዕመናን በቤተሰብ ደረጃ እንዲያመልክ መደረጉን አመልክቷል።

የኢትዮጵያ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ፓስተር ተመስገን ብርሃኑ እንደገለጹት፤ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚደረግ እንቅስቃሴ ከእምነት ጋር የሚጋጭ ነገር የለውም።

ምእመኑ በቤቱ ሆኖ የአምልኮ ስነስርዓቱን መከወን እንደሚችል ገልጸዋል።

የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የህብረት አምልኮ ሙሉ በሙሉ እንዲቆም በማድረግ ምእመኑ በቤተሰብ ደረጃ እንዲያመልክ መመሪያ መተላለፉን ፓስተር ተመስገን ተናግረዋለ።

ቫይረሱን አስመልቶ ከተለያዩ የመድረክ አገልጋዮች የሚቀርቡ የተሳሳቱ መረጃዎች ምዕመኑ ሳይቀበል መቀበል እንደለሌበትና የጤና ባለሙያዎች የሚያስተላልፉትን መልዕክት እንዲተገብር ፓሰተር ተመስገን አሳስበዋል።

የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የቃለ ህይወት ቤተ ክርስቲያን ብዙ ህዝብ የሚገኝበትን የአምልኮ ስርዓት ሙሉ በሙሉ እንዳቆመች የቤተ ክርስቲያኗ ጸሀፊ አቶ ስምኦን ሙላቱ ተናግረዋል።

በቫይረሱ ምክንያት ለችግር ሊዳረጉ የሚችሉ አቅመ ደካሞችን ምእመኑ እንዲደግፍ በቤት ክርስቲያኒቱ በኩል መልዕክተ መተላለፉን ጠቁመዋል።

እንደ ቃለ ህይወት ቤተ ክርስቲያን አማኞች በቤታቸው በመሆን ርቀታቸውን ጠብቀው እንዲያመልኩ መመሪያ መተላለፉን ገልፀዋል።

በቤተሰብ ደረጃ የአምልኮ ስርዓት እንዲከናወን ከቤተ ክርስቲያኖች አንድ አይነት መልዕክት መተላለፉ የሚደነቅ እና የፖሊስን ስራ የሚያቀል እንደሆነ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል እንዳሻው ጣሰው ተናግረዋል።በካውንስሉ በኩል   የተሰሩት ስራዎች የሚበረታቱና ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተናግሯል።

የአዲስ አበባ መልካም ጅማሬዎችን መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም ወደ ምዕመኑ ማድረስ እንዳለባቸው ዲያቆን ዳንኤል ጠቁመዋል።

የሀይማኖት ተቋማት ለእምነት ተከታዮቻቸው ምእመናን የኮሮናቫይረስ መሰረታዊ መረጃዎችና ቅድመ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በማስገንዘብ በሽታውን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው ከመንግስት በኩል መልዕክት መተላለፉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም