ምዕራብ ኦሮሚያን የልማትና የምርት ማዕከል ለማድረግ ይሰራል - ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ - ኢዜአ አማርኛ
ምዕራብ ኦሮሚያን የልማትና የምርት ማዕከል ለማድረግ ይሰራል - ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ መጋቢት 24/2012 (ኢዜአ) ቀደም ባሉት ዓመታት ትኩረት ተነፍገው የቆዩትን የምዕራብ ኦሮሚያ ዞኖች የልማትና የምርት ማዕከል ለማድረግ በስፋት እየተሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።
በፕሬዚዳንቱ የተመራ ከፍተኛ የክልሉ መንግስት የስራ ኃላፊዎችን ያከታተ ቡድን በአራት የወለጋ ዞኖች ጉብኝት አድርጓል።
ቡድኑ በአካባቢዎቹ በነበረው የጸጥታ ችግር ምክንያት ተቋርጠው የነበሩና ዳግም ግንባታቸው የተጀመሩ የመሰረተ ልማት ስራዎችን ጎብኝቷል።
ፕሬዚዳንቱ እንደሚሉት፤ አካባቢው በተለያዩ ምክንያቶች ቀድሞውንም ከሌሎች የኦሮሚያ ዞኖች ተለይቶ ትኩረት የተነፈገው ነው።
''በተለይ ደግሞ አካባቢው በተፈጠሮ ኃብት የታደለ ቢሆንም ከፍተኛ የመንገድ፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ችግርና የኤሌክትሪክ ችግር አለበት'' ብለዋል።
''ይህ መሆኑ ደግሞ አካባቢው ተፈጥሮ ከቸረችው ኃብት ተጠቃሚ ሳይሆን ቀርቷል'' ያሉት አቶ ሽመልስ፤ በአሁኑ ወቅት የክልሉ መንግስት ልዩ ትኩረት እንደሰጠው አመላክተዋል።''ቅድሚያ በአካባቢው ያለውን ኃብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል ከተቻለ በአካባቢው ያሉ ዜጎችን ህይወት በመሰረታዊነት መቀየር ይቻላል'' ብለዋል።
ፕሬዚዳንቱ ባጋጠመው የጸጥታ ችግር የተነሳ ተቋርጠው ከነበሩት የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች መካከል አንዱ የደንቢ ዶሎ አየር መረፊያ መሆኑን አስታውሰዋል።
አሁን ግን በአካባቢው ሰላም በመምጣቱ የአየር ማረፊያው የማስፋፊያ ስራ ተጠናቆ በቅርብ ጊዜያት አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ጠቁመዋል።
የአየር ማረፊያው ስራ መጀመር በአካባቢው የሚገኘው የልዩ መስህቦች ባለቤት የሆነው የናቲ ወለል ፓርክ እንዲጎበኝና የቱሪስቶች እንስቃሴን እንዲያድግ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው እምነታቸውን ገልጸዋል።
በጥቅሉ ይህ የመጓጓዣ ዘዴ ማህበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ እንቅስቃሴን በማንቃቃት ረገድ ትልቅ አቅም እንደሚሆን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
''ከዚህ ጎን ለጎን የክልሉ መንግስት ከፌዴራል መንግስት ጋር በመሆን ምዕራብ ኦሮሚያን የሚያስተሳስሩ 13 የመንገድ ፕሮጀክቶችን ይዟል'' ብለዋል።
የእነዚህ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ በሚጠናቀቅበት ወቅት የአካባቢው ሕዝብ በቀላሉ ምርቱን ወደ ገበያ አቅርቦ ተጠቃሚ እንዲሆን እንደሚያስችለውም ተናግረዋል።በቀጣይም መንግስት በምዕራብ ኦሮሚያ የጀመረውን የልማት ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ሽመልስ ገልጸዋል።
በፕሬዚዳንቱ የተመራው የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ቡድን በአካባቢው ቄለም ወለጋ፣ ምዕራብ ወለጋ፣ ምስራቅ ወለጋና ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞኖችን መጎብኘቱ ይታወቃል።