የአዲስ አበባ ከተማ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ አምስት አዳዲስ ግንባታ ሊጀምር ነው

131
አዲስ አበባ ሰኔ 24/2010 የአዲስ አበባ ከተማ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ አምስት አዳዲስ ግንባታ ለመጀመር መሰረተ ድንጋይ ሲያስቀምጥ ግንባታቸው የተጠናቀቁትም ተቋማትም አስመርቋል፡፡ ከንቲባ ዲሪባ ኩማ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በአገሪቷ ልዩ ትኩረት ተስጥቶት እየተሰራ ይገኛል። በዛሬው ዕለትም የማኑፋክቸሪንግ ስልጠና ወርክሾፖች፣ የቴክኖሎጂ ማዕከላት፣ የኢንኩቤሽና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማዕከላት ግንባታ ምርቃትና  አምስት አዳዲስ የሚገነቡ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት የመሰረት ድንጋይ አስቀምጧል። የማኑፋክቸሪንግ ስልጠና ዘርፍ የበቃ የሰው ኃይል ለማፍራትና ቴከኖሎጂን ለማሸጋገር የሚያስችል የጨርቃጨርቅ፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ ብረታ ብረት እንዲሁም የአግሮ ፕሮሰሲንግ ግንባታ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል። በከተማዋ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ 11 ዘመናዊ የማኑፋክቸሪንግ ኮሌጆችና ወርክ ሾፖች በብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን  አማካይነት ግንባታና የተሟላ የማሽን ተከላ በማከናወን በ2009 ስልጠና መስጠት መጀመራቸውን ያስታወሱት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘርዑ ስሙር ናቸው። በዚህም በዘርፉ ይታይ የነበረውን የስልጠና ችግር ለመፍታት ተችሏል ብለዋል። በ2010 በጀት ዓመት በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የበቃ የሰው ኃይል ለማፍራትም ባለ ሁለት ወለል ህንጻ በመገንባት በአግሮ ፕሮሰሲንግ የአትክልትና የፍራ ፍሬ ጭማቂ ዝግጅት የስልጠና የሚሰጡ ወርክሾፖች መገንባቱን ገልጸዋል። በተመሳሳይ  በ5 ክፍለ ከተሞች የቴክኒክና ሙያ ተደራሽነት ለማረጋገጥ 5 አዳዲስ የፖሊቴክኒክ ኮሌጆችን ለመገንባት የመሰረተ ድንጋይ መቀመጡን ጠቁመዋል። በዚህ ዓመት የተቋሙ የማሰልጠን አቅም ከ30 ሺህ በላይ ደርሷል ነው ያሉት አቶ ዘርዑ። ይህም ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰው ኃይል በጥራትና በብዛት ለማፍራት እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግር  ለማምጣት ከፍተኛ ተነሳሽነትን ይፈጥራል ያሉት ኃላፊው፤ የተገነቡ የኢንዱስትሪ ወርክሾፖች በ2011 ወደ ስራ ይገባሉ ብለዋል። በተጨማሪም 13 ኮሌጆችን የሚያስተሳስር የኢንፎርሼን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማት የተገነባ ሲሆን ቀልጣፋ አሰራር ለመዘርጋት እና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ለማስተሳሰር የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል። የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማትን ምቹ ለማድርግ በተቋማቱ ውሰጥ የሚገኙትን የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎችና ሰራተኞችን የማስልጣን ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል። አዳዲስ ግንባታ ለማካሄድ መሰረተ ድንጋይ የተጠለባቸውም ሳይቶች  የኮዬ ፈጬ፣ ቦሌ ለሚ፣ የካ አባዶ፣ ኮልፌ አለም ባንክ አካባቢና ንፋስ ስልክ ጀሞ ወይም ለቡ ናቸው። የማስፋፊያ ግንባታቸው የተጠናቀቁ ተቋማት ደግሞ እንጦጦ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ፣ ምስራቅ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ፣ አቃቂ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ፣ ንፋስ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ፣ ተግባረዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እና ጄኔራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ  ናቸው።          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም