ቤተ ክርስቲያኗ ምዕመናንና ካህናት በቤታቸው ተወስነው እንዲጸልዩ ወሰነች

110

አዲስ አበባ መጋቢት 23/2012  (ኢዜአ) ከተወሰኑ አገልግሎት ሰጪ ካህናት ውጪ ምዕመናንና ካህናት በቤታቸው ተወስነው እንዲጸልዩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ወሰነች። 
ቤተ-ክርስቲያኗ በኮሮና ቫይረስ ቅድመ ጥንቃቄና በምትሰጠው ድጋፍ ዙሪያ መግለጫ ሰጥታለች።   

የቋሚ ሲኖዶስ ዋና ጸሀፊና የምስራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ  በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ ቋሚ ሲኖዶሱ ከተወሰኑ ካህናት ውጪ ምዕመናንና ሌሎች ካህናት በቤታቸው እንዲቆዩ ውሳኔ አሳልፏል።      

አገልግሎት የሚሰጡ ካህናት ምግብ እየቀረበላቸው ከቤተ ክርስቲያናት ቅጥር ግቢ ሳይወጡ መንፈሳዊ ግልጋሎት እንዲሰጡ ተወስኗልም ነው ያሉት።    

አቡነ ዮሴፍ እንደተናገሩት፤ ቤተ-ክርስቲያኗ የለይቶ ማቆያ ቦታዎችን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት ያደረገች ሲሆን በቤተ ክርስቲያኗ ስር የሚገኙ መንፈሳዊ ኮሌጆች፣ የካህናት ማሰልጠኛዎችና ዘመናዊ ትምህርት ቤቶች ለዚሁ አገልግሎት እንዲውሉ ፈቅዳለች።  

''በመንግስት በኩል በሽታውን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የመንበረ ፓትሪያሪክ ሦስት ሚሊዮን ብር በጊዜያዊነት ድጋፍ ተደርጓል'' ያሉት ዋና ጸሀፊው፤ ''በቤተክርስቲያኗ ስር ለሚገኙ ህጻናትና ተረጂዎች በተስፋ ግብረ ኃይል በኩል የምግብ፣ የንጽህና መጠበቂያና ሌሎች ድጋፎችን የማሰባሰብ ተግባራት ይከናወናሉ'' ብለዋል።

ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ከመጋቢት 23 ቀን 2012 ዓም ጀምሮ ሱባኤ ገብተው በጾምና በጸሎት እንዲቆዩ መወሰኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም