ብሔራዊ ባንክ አዲስ የክፍያ ስርዓት መመሪያ አወጣ - ኢዜአ አማርኛ
ብሔራዊ ባንክ አዲስ የክፍያ ስርዓት መመሪያ አወጣ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2012 ( ኢዜአ)የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አሁን ያለውን የክፍያ ስርዓት ውጤታማነት በከፍተኛ ደረጃ ያሳድጋል ያለውን አዲስ የክፍያ ስርዓት መመሪያ አወጣ።
ለክፍያ መሳሪያዎች አቅራቢዎች ፈቃድና ስልጣን የሚሰጠው ይህ መመሪያ ከዛሬ ጀምሮ ስራ ላይ እንደሚውል ብሔራዊ ባንክ ገልጿል።
በባንኩ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ተፈርሞ የጸደቀው መመሪያ የክፍያ መሳሪያዎችን ፈጠራ በማበረታታት የፋይናንስ አገልግሎትን በማቀላጠፍና በማሳደግ ረገድ ጠቃሚ ይሆናል ተብሎ እምነት ተጥሎበታል።
መመሪያው ግልጽና አስቻይ የሆነ የቁጥጥር ስርዓት የሚፈልግ እንደሆነ የገለጸው ባንኩ፤ የክፍያ መሳሪያዎቹ የተገልጋዮችን ፍላጎት እንደሚያስጠብቅ አመልክቷል።
ፈቃድ ካላቸው ተቋማት ውጭ የክፍያውን መሳሪያ ለማግኘት የሚፈልግ አካል በብሔራዊ ባንክ የተዘጋጀውን የማመልከቻ ቅጽ በመሙላት ፈቃድ ማግኘት እንደሚችሉ ተጠቁሟል።
በዚሁ መሰረት በባንኩ የተረጋገጠ ፈቃድ የተሰጣቸው የክፍያ መሳሪያው አቅራቢዎች ገንዘብ ወጪና ገቢ ማድረግ፣ የአገር ውስጥ ሃዋላን ጨምሮ የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ያስችላል።
በብሔራዊ ባንኩ በተሰጠ የጽሁፍ ፈቃድ መሰረት የክፍያ ስርዓቱ አቅራቢዎች አገልግሎታቸውን ለሌሎች በውክልና ሊሰጡ እንደሚችሉ በመመሪያው ተቀምጧል።
የፋይናንስ ስርዓቱ ላይ ስጋት የሚያስከትሉ ጉዳዮችን ለመከላከል ሲባል ብሔራዊ ባንኩ የክፍያ ስርዓቱ አቅራቢዎችን፣ ወኪሎችና ሌሎች አብረው የሚሰሩ አካላትን እንደሚቆጣጠር መመሪያው አስቀምጧል።