ቀጥታ፡

በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 29 ደረሰ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 23/2012  (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 29  መረድረሱን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት  እንዳስታወቀው ይህ መረጃ እስከ ተጠናቀረበት ሰአት ባለፉት 24 ሰዓት ውስጥ 68 የላብራቶሪ ምርመራ  በማድረግ  በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ተጨማሪ ሶስት (3) ሰዎች መገኘታቸውን አረጋግጧል።

ይህም  በሀገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርን ሃያ ዘጠኝ (29)  ማድረሱን በጠቆም፤ በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጡት ሶስት ግለሰቦች ሁሉም ኢትዮጵያዊያን መሆናቸው ተገልጿል፡፡

 የመጀመሪያዋ ታማሚ የ33 አመት ሴት ስትሆን የጉዞ ታሪኳ ጅቡቲ፣ ብራዚል፣ ህንድ እና የመጨረሻ በረራዋ ኮንጎ ብራዛቪል ሲሆን፤ የበሽታውን ምልክት በማሳየቷ በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆና በተደረገላት የላብራቶሪ ምርመራ በኮሮና ቫይረስ የተያዘች መሆኗ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

ሁለተኛው ታማሚ የ 26 ዓመት ወንድ ሲሆን የስራ ባህሪው ከተለያዩ ተጓዥ መንገደኞች ጋር ግንኙነት ያለው ሲሆን የበሽታውን ምልክት በማሳየቱ በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆኖ በተደረገለት የላብራቶሪ ምርመራ በኮሮና ቫይረስ መያዙ ተረጋግጧል፡፡

 ሶስተኛው ታማሚ የ32 ዓመት ወንድ ሲሆን ቀደም ብሎ በበሽታው መያዙ ከተረጋገጠ ሰው ጋር ግንኙነት የነበረውና በለይቶ ማቆያ ውስጥ ሆኖ ክትትል ሲደረግለት የነበረ ሲሆን በተደረገለት የላብራቶሪ ምርመራ በቫይረሱ መያዙን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

ሶስቱም ታማሚዎች በለይቶ ህክምና መስጫ ማዕከል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ሲሆን ከታማሚዎቹ ጋር ግንኙነት የነበራቸውን ሌሎች ሰዎች የመለየት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በአሁኑ ሰዓት በለይቶ ህክምና መስጫ ማዕከል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ያሉ ሃያ አምስት (25) ታማሚዎች ሲኖሩ ሁለት ታማሚዎች በጽኑ ህሙማን ህክምና ክፍል ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡

ከዚህ በፊት እንደተገለጸው ሁለት ታማሚዎች ሙሉ በሙሉ አገግመዋል፡፡ ነገር ግን ለጥንቃቄ ሲባል በለይቶ ማቆያ ክትትል እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡

ህብረተሰቡ የበሽታውን ስርጭት ግምት ውስጥ በማስገባት የመከላከያ መንገዶችን እና ከመንግስት የሚተላለፉ እርምጃዎችን ትኩረት በመስጠት እንዲተገብርም ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም