ቀጥታ፡

በኮሮና ቫይረስ የተያዘ አንድ ተጨማሪ ሰው መገኘቱን ጤና ሚኒስቴር ገለጸ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 22/2012( ኢዜአ)የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዛሬ ባካሄደው ተጨማሪ የላብራቶሪ ምርመራ አንድ በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሰው በማረጋገጡ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ሃያ ስድስት (26) መድረሱን ጤና ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

በቫይረሱ መያዙ የተረጋገጠው ግለሰብ የ42 ዓመት የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪ የሆነ ኢትዮጵያዊ ሲሆን የአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ከመጀመሩ አስቀድሞ መጋቢት 9/2012 ከአውስትራሊያ አዲስ አበባ እንዲሁም መጋቢት 10/2012 ከአዲስ አበባ ወደ ድሬዳዋ ተጉዟል፡፡

ግለሰቡ የበሽታው ምልክት በማሳየቱ በላብራቶሪ ምርመራ በቫይረሱ መያዙ የተረጋገጠ ሲሆን፤በአሁኑ ሰዓት በድሬዳዋ የለይቶ ህክምና መስጫ ማዕከል የህክምና እርዳታ እየተደረገለት እንደሆነም ተገልጿል፡፡

በሀገሪቱ በአሁኑ ሰአት በለይቶ ህክምና መስጫ ማዕከል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ያሉ ሃያ ሁለት (22) ታማሚዎች ሲኖሩ ሁለት ታማሚዎች በጽኑ ህሙማን ህክምና ክፍል ክትትል እየተደረገላቸው ነው ተብሏል፡፡

ህብረተሰቡ የበሽታውን ስርጭት ግምት ውስጥ በማስገባት የመከላከያ መንገዶችን እና ከመንግስት የሚተላለፉ እርምጃዎችን ትኩረት በመስጠት እንዲተገብርም ሚኒስቴሩ አሳስቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም