የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ሁሉም እንዲረባረብ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ጥሪ አቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ሁሉም እንዲረባረብ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ጥሪ አቀረበ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 22/2012(ኢዜአ) የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ሁሉም እንዲረባረብ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ጥሪ አቅርቧል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬተሪያት ሃለፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል እየተሰራ ያለውን ስራ በሚመለከት መግለጫ ሰተዋል።
በመግለጫቸውም፤ የኮሮናቫይረስ ስርጭት ከአዲስ አበባ ውጪ በክልል ከተሞች መከሰቱን ተናግረው የተገኙት ሰዎች የውጪ አገር የጉዞ ታሪክ የነበራቸው ከአሜሪካ እና ዱባይ የመጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አጠቃላይ በአገሪቱ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 25 መድረሱንም ተናግረዋል።
የበሽታውን ስርጭት ለመግታተ ህዝብና መንግስት ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ስለመሆኑ የተናገሩት አቶ ንጉሱ በዚህ መሰረት በክልሎች እስካሁን 150 የለይቶ ማቆያ እና የህክምና መስጫ ቦታዎች ተዘጋጅተዋል ብለዋል።
በአዲስ አበባና ፌደራል ደረጃ ደግሞ 170 ተቋማት መዘጋጀታቸውንና እነዚህም ህክምናን ጨምሮ የማቆያ አገልግሎት የሚሰጥባቸው መሆኑን አስረድተዋል።
ማቆያዎቹ በአጠቃላይ 176 ሺህ ዜጎችን ለማስተናገድ በሁሉም መንገድ ዝግጁ ናቸው ብለዋል።
ህብረተሰቡ ስለበሽታው ያለው ግንዛቤ ከእለት ወደ እለት አየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም በገበያ፣ በትራንስፖርት፣ በመዝናኛ ቦታዎች እና ሀይመኖታዊ ተቋማት አሁንም መዘናጋት ይስተዋላል ብለዋል።
የሀይማኖት አባቶች፣ አርቲስቶች፣ የመንግስት ስራ ሃላፊዎች፣ የመገናኛ ብዙሃን ጨምሮ በርካታ አካላት በሃላፊነት እየሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።
የፀጥታ እና የህግ ማስከበረ እንቅስቃሴው በተጠናከረ ሁኔታ ለማስኬድ የፀጥታ መዋቅሩ ህግና ስርዓት ማስከበር እና የቫይረሱን ጫና ለመቋቋም እንቅፋት የሚሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ስራ እየሰራ እንደሚገኝም እንስተዋል።
ከእነዚህ ውስጥ በቦሌ አየር ማረፊያ በኩል የሚመጡ ዜጎችን በማጓጓዝ ደህንነታቸው ተጠብቆ በማቆያ እንዲቀመጡ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል።
በመሰረተ ልማት የተቋማትና የድንበር አካባቢ ጥበቃና ፍተሻ እንዲሁ ተጠናክሮ መቀጠሉንና የጭፈራ፣ መጠጥ እና ሺሻ ቤቶች ክትትል በማድረግ እንዲዘጉ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ይህንን መጥፎ ወቅት እንደ ጥሩ አጋጣሚ ተጠቅመው የንግድ ስርዓቱን በማዛባት ስራ ላይ የተሰማሩ ከ7 ሺሀ በላይ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱንም አስታውሰዋል።
ህብረተሰቡ በመደጋገፍ ረገድ እያደረገ ያለው አስተዋፆ ተጠናክሮ እየቀጠለ ስለመሆኑ አንስተው በአጭር ጊዜ ውስጥ በተቋቋመው ኮሚቴ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ማሰባሰብ መቻሉን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በውጪ ካሏት 60 ኤምባሲዎች 41 ኤምባሲዎች ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ሰራተኞች የወር ደመወዛቸውን ለመለገስ ቃል መግባታቸውንም ጠቅሰዋል።
በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንም የተቻላቸውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን አንስተዋል።
በተለይም ቻይና እና አቡዳቢ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ከ4 ሚሊዮን ብር በላይ መገኘት መቻሉንም ተናግረዋል።
በቀጣይም ገንዘብ መደገፍ የሚፈልጉ አካላት በቼክ ሳይሆን በጥሬው በተገለፁት የባንክ አካውንቶች ብቻ ገቢ እንዲያደረጉ ጠይቀዋል።
ለአገር ውስጥ እና ለውጪ ባለሀብቶች ለግንኙነት ያመች ዘንድ የኮሚቴ አደረጃጀቱ ለአገር ውስጥ እና ለውጪ ተብሎ መደራጀቱንም አቶ ንጉሱ አንስተዋል።
በመጨረሻም ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ችግር ለመውጣት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ እንዲረባረብ ነው አቶ ንጉሱ የጠየቁት።